6ኛው የኢትዮጵያ ፓትረያሪክ
ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማይ ፓትረያሪክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘ ኢትዮጵያ |
የክርስትና እና የእስልምና ኃይማኖቶች ሂደትና ውጤት ከኢትዮጵያ ማንነት
ተነጥሎ የሚታይ አይደለም፡፡ በዚህ ረገድ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ዛሬ ትደርስ ዘንድ ከፍተኛውን አስተዋጾ በመወጣት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ
ቤተ ክርስቲያን ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ዓለም ኢትዮጵያን ከቤተ ክርስቲያኗ እሴቶች ጋር በአንድ ሊመለከት የቻለበትም ሚስጥር ሀገሪቱና
ቤተ ክርስቲያኗ በዘመናት ሂደት ከፈጠሩት አብሮነት የተፈጠረው ኢትዮጵያ ገናና ታሪክ በመነሳት ነው፡፡
5ኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትረያሪክ የነበሩት
ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ቀዳማይ፤ ፓትረያሪክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘ ኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘ አክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ
ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያኗን በዓለም አደባባይ የቀደመ ክብሯ ስፍራውን እንዲይዝ አድርገው የ20ኛ ዓመት በዓለ ሲመታቸውን ባከበሩ
ማግስት ነበር ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት፤ ይህንን ተከትሎ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ፕሬዝዳንትና የአለም ኃይማኖቶች የክብር
ፕሬዝዳንት የነበሩት የኢትዮጵያ ፓትረያሪክ ሞት የዓለም ትኩረት ሳበ፤ ይህ ትኩረት እስከ 6ኛው ፓትረያሪክ ምርጫና የምርጫ ሂደት
ድረስ የመገናኛ ብዙሃንን ትኩረት እንደሳበ ቀጥሎ ነበር፡፡
የካቲት 21 ቀን 2005 ዓ.ም የተደረገው ምርጫ ከአምስት ብጹአን
ጳጳሳት ውስጥ ብጹእ አቡነ ማትያስን ፓትረያሪክ የሚያደርግ ውጤት አመጣ እናም ቅዱስነታቸው የካቲት 24 ቀን 2005 ዓ.ም ብጹአን
ጳጳሳት፣ የእምነት አባቶች፣ አምባሳደሮች፣ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትና በርካታ እንግዶች በተገኙበት በዓለ ሲመታቸው ተካሄደ፡፡
አባታቸው አቶ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ማርያም እናታቸው ደግሞ ወ/ሮ
ከለላ ገ/መስቀል ይባላሉ፡፡ ከእነዚህ ሁለት ጥንዶች በትግራይ ክፍለ ሀገር በቀድሞ አጠራር አጋሜ አውራጃ ጥር 15 ቀን 1934
ዓ.ም ተወለዱ፡፡ የትውልድ ቀያቸው ልዩ ስም እግዚእ ሐጸራ ይባላል፡፡ ትምህርትን ሀ ብለው የጀመሩት ከአጎታቸው ከቀሲስ ወልደ ገሪማ
እግር ስር ተቀምጠው ነበር፡፡ ከዚያም ቀጠሉ ከትውልድ ቀያቸው ወደ ተንቤን በማቅናት መካነ ህይወት ጭሕ ገዳም ገቡ፡፡ በዚህ ገናና
ገዳም ቆይታቸው ከየኔታ መንግስተ አብ ገብረ ማርያም ዲቁና፣ ቅስና ባህረ ሃሳብን አጠኑ፡፡ የባህረ ሃሳብ ትምህርት ቀናትን በቁጥር
የሚያሰላ ከፍተኛ ጥበብ በመሆኑ እርሱን ከተወጡ በኃላ ከመዝገበ ቅዳሴ መምህሩ ከየኔታ ተስፋ ማርያም ገብረ ማርያም ጉባኤ ተቀላቅለው
መዝገበ ቅዳሴን በማጥናት በመምህርነት ተመረቁ፡፡
የዚህ ገዳም ቆይታቸው ከአያሌ ትምህርቶች ጋር በእጅጉ እንዲተዋወቁ
አድርጓቸዋል፤ ከያሬዳዊ ዜማ መምህሩ ከመምህር ገብረ ስላሴ ኃ/ማርያም ዘንድ ምዕራፍና ጾመ ድጓን ከነሙሉ ጓዙ አጠኑ፤ ከቅኔው መምህር
ከየኔታ ዕንቁ ባሕረይ አስረስ የቅኔ ጉባኤ ገብተው ቅኔን ተማሩ፤ ከዚያ በኃላ ነው ፊታቸውን ወደ መጻህፍት ትርጓሜ ያዞሩት፤ ቅዱስነታቸው
እድሜአቸውን በትምህርት ያሳለፉ አባት ናቸው ለማለት ይቻላል፡፡ በመጻህፍት ቤት ውዳሴ ማርያምን፣ ቅዳሴ ማርያምን፣የ የኪዳንንና
ትምህርተ ህቡአትን ከየኔታ ስብሐት ለአብ እግር ስር ተቀምጠው ተማሩ፡፡
12 ዓመታትን በገዳም ገዳማዊ ኑሮንና የተለያዩ ትምህርቶችን ካጠኑ
በኃላ የገዳሙ አብምኔት ከነበሩት ከመምህር አሥራተ ጽዩን ኮከቡ ምንኩስናን ተቀበሉ፡፡ ከዚያም ይበልጥ ቤተ ክርስቲያንን የማገልገል
ስራ ጥሪያቸው ሆነ ትምህርታቸውና ህይወታቸው ምስክር ሆኖ በወቅቱ የትግራይ ክፍለ ሀገር ከነበሩት ከብጹእ አቡነ ዩሐንስ መዐርገ
ቅስናን ተቀበሉ፡፡
ከአደጉበትና ከተማሩበት ገዳም የወጡት በ1957 ዓ.ም ነበር፡፡ በመጀመሪያ
ያቀኑት ወደ ርዕሰ አድባራት አክሱም ጽዮን ገዳም ነበር፤ በዚያም ከእውቁ መምህር ከየኔታ ገብረ ጊዮርጊስ ገብረ እግዚእ ጉባኤ መጽሐፈ
ሐዲሳትን ተማሩ፤ ከዚያም በ1961 ዓ.ም ወደ ጎንደር በመጓዝ አራት ዓይና በመባል ከሚጠሩት ከታላቁ ስመ ጥር ከዶክተር ዓየለ ዓለሙ
ጉባኤ በመግባት አክሱም የጀመሩትን የመጻሐፍተ ሀዲሳት ትምህርት አጠናክረው በ27 መጻሐፍተ ሐዲሳት በአስተማሪነት ተመረቁ፡፡
በጎንደር በነበሩበት ጊዜ ጻድቁ ዩሐንስ ትምህርት ቤት ዘመናዊ ትምህርትን
ሲከታተሉ ቆይተዋል፡፡ በ1968 ወደ አዲስ አበባ ከመጡ በኃላ የብጹእ አቡነ ተክለሃይማኖት አቡነ ቀሲስ እና ም/ልዩ ጸሐፊ በመሆን
አገልግለዋል፡፡ ከዚያም በ1971 ዓ.ም በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ኤጲስ ቆጶስ በመሆን ተሾሙ፤ ከ3 ዓመት በአገልግሎት በኃላ
ግን ችግር ወደ አሜሪካ እንዲሰደዱ አስገደዳቸው፤ በዚያም ሳሉ ግን
15 ዓመታትን መንፈሳዊ አገልግሎት በመስጠት ነበር ያሳለፉት፤ በድጋሚ በ1999 ዓ.ም በቅዱስ ሲኖዶስ ፍቃድ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው
በዚያ የኢትዮጵያ ገዳማት ሊቀ ጳጳስ በመሆን በርካታ መንፈሳዊ ስራዎችን ሲያከናውኑ ቆይተዋል፡፡
ከዚያም በየካቲት 2005 ዓ.ም 6ኛውን የኢትዮጵያ ፓትረያሪክ ለመምረጥ
በነበረው ሂደት እነሆ እጩ ለመሆን በቁ፤ በሰሜን አሜሪካ ያከናወኑትን መንፈሳዊ አገልግሎት ጨምሮ፣ ምእመናንን በወንጌል ትምህርት
በማጽናናት፣ የቤተ ክርስቲያን አንድነት እንዲረጋገጥ በመድከም፣ አብያተ ክርስቲያናት እንዲቋቋሙ በማድረግ፣ የወጣቱን መንፈሳዊ እንቅስቃሴ
በማጠናከር፣ የቤተ ክርስቲያኗ እውነተኛ ትምህርት እንዲጠበቅ በማድረግ፣ በርካታ ስራዎችን ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ ከትግርኛ ግእዝና አማርኛ
ቋንቋዎች በተጨማሪ እንግሊዘኛ እብራይስጥና አረብኛ ቋንቋዎችን የሚችሉት እኒህ አባት የካቲት 21 ቀን 2005 ዓ.ም ተካሂዶ በዚያው
ቀን የቆጠራ ውጤቱ በታወቀው የ6ኛው ፓትረያሪክ ምርጫ 806 መራጮች ከሰጡት ድምጽ 500 በማምጣትና በከፍተኛ ውጤት ተመርጠው የካቲት
24 ቀን 2005 ዓ.ም በመንበረ ጽባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ባዓለ ሲመታቸው ተካሂዷል፡፡ 6ኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ
ቤተ ክርስቲያን ፓትረያሪክ የ71 ዓመቱ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማይ ፓትረያሪክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘ ኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ
ዘ አክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ኃይማኖት፤
No comments:
Post a Comment