የቱሪዝም ፀጋ በቤንች ማጂ
ቱሪዝም በአሁኑ ሰዓት በቤንች ማጂ
ዞንም በከፍተኛ ፍጥነት በማደግ ላይ ይገኛል፡፡ ዘርፍ ደህንነት ቀናሽ በመሆኑ ለዜጎች በተለይም ለሴቶችና ለወጣቶች የስራ ዕድል
ይፈጥራል፡፡ በመሆኑም የደቡብ ምዕራብ ዞኖች ፈርጥ በሆነችው ቤንች ማጂ ዞን
በእንግዳ ተቀባይነቱ የሚታወቅ ህዝብ ማእከል ከመሆኗ ጋር
ተዳምሮ የዞኑ ብሔረሰብና ህዝቦች መልካም እሴት ታክሎት ዞኑን የቱሪስት መዳረሻ ከማድረጉም በላይ ለሀገርና ለውጭ ሀገር ቱሪስቶች
የተሟላ አገልግሎት የሚሰጡ የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በጥራትና በብዛት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ መጥቷል፡፡ በመሆኑም በዞኑ
ቀልብን የሚስቡና የሚማርኩ በርካታ ተፈጥሮአዊ ፣ ባህላዊና ታሪካዊ መስህቦች ሲገኙ የተወሰኑትን ለመቃኘት እንሞክራለን፡፡
ኦሞ ብሔራዊ ፓርክ
የኦሞ ብሔራዊ ፓርክ በቤንች ማጂ
ዞን በማጂ ወረዳ በሙይ ቀበሌ የሚገኝ ሲሆን የክልሉ ትልቁ ፓርክ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ በ870 ኪሎ ሜትር ከሚዛን ከተማ 242
ኪሎ ሜትር ከማጂ ከተማ ደግሞ 70 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ የኦሞ ፓርክ ልዩ ልዩ የዱር እንሰሳትና ዕፅዋቶች ሲገኙበት
የተለያዩ 75 አጥቢዎች 325 አእዋፍ ዓይነቶች ይገኙበታል፡፡ በፓርኩ ውስጥ በሺ የሚቆጠሩ ውድንቢዎች፣ የመጋላ ቆርኪ መንጋ፣ ሳላዎች፣
የሜዳ ፍየሎች ወዘተ ይገኛሉ፡፡ ውድንቢ በኢትዮጵያ በኦሞ ብሔራዊ ፓርክ ብቻ የሚገኝ የዱር እንሰሳ ነው፡፡ ያሉበት አካባቢ በባለሙያ
የተጠረቡ በሚመስሉ የድንጋይ ንጣፍ የተነጠፈና በለመለሙ ቄጤማዎች ያሸበረቀ ነው፡፡ በስፍራው የተለያየ የሙቀት መጠንና ጣዕም ያላቸው
ፍል ውኃዎች መኖራቸው ለተመራማሪዎች የምርምርና ለባለሀብቱ ደግሞ
የኢንቨስትመንት መስክ ይከፍታል በሚል ኦሞ ፓርክን የመጪው ጊዜ የልማት ቀጠና አስብሎታል፡፡
የኡሱቃ ፍል ውኃ
የኡሱቃ ተፈጥሮ ፍል ውኃ በሸኮ
ወረዳ በሸሚ ቀበሌ ይገኛል፡፡ መስህቡ ከዞኑ ርእሰ ከተማ በ31 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ በስፍራው ከ44 የሚበልጡ እና
ያለማቋረጥ የሚፍለቀለቁ ፍል ውኃዎችን ይዟል፤ የመስህቡ አከባቢ በተፈጥሮ ያሸበረቀና በጥቅጥቅ ደኖች የተከበበ ነው፡፡
የወጀምታ ፍል ውኃ
ይህ ፍል ውሃ በጉራፈረዳ ወረዳ
በወጀምታ ቀበሌ ልዩ ስሙ አሮጌ ብርሃን አካባቢ ይገኛል፡፡ ፍል ውሃው ከሚዛን ከተማ በ47 ኪ/ሜትር ርቀት ላይ ሲገኝ ከ6 ኪሎ
ሜትር የእግር መንገድ በስተቀር በበጋም ሆነ በክረምት በማንኛውም ተሸከርካሪ የሚያደርስ መንገድ አለው፡፡
የወጀምታ ፍል ውኃ እስኪደርሱ ድረስ
እግረ መንገድዎን የበበቃ ቡና ተክል ፕሮጀክትና በውስጡ ያቀፋቸውን ትሩፋቶች መልካአ ምድሩንና የተፈጥሮ ደኑን እያደነቁ ይጓዛሉ፡፡
ፍልውኃውን ለየት ከሚያደርጉትና ቀልብን ከሚገዙት ውስጥ ፍል ውኃው ከሶስት ግዙፍ የድንጋይ ቋጥኞች አካላት ላይ በተለያዩ አቅጣጫዎች
ይፈሳል፡፡ ከአንደኛው ቋጥኝ አናት ላይ ያለው ፍል ውሃ ድስት ላይ እንደተጣደ ውሀ ሲፍለቀለቅ ማየቱ ቀልብን ይስባል፡፡ የመስህቡ
ዙሪያ ቀጫጭን ሐምራዊ ቀለም ባላቸው ቄጠማዎች ከማሸብረቁም በላይ ዙሪያው ጥቅጥቅ ባሉ ደኖች የተዋበና ያማረ ነው፡፡
የወርጉ ገዳም
ዋሻ
ወርጉ ገዳም ዋሻ በሸኮ ወረዳ በሳንቃና
ወርጉ ቀበሌ ድንበር ላይ ከሚዛን ከተማ በ22 ኪ/ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ የመስህቡ አካባቢ እጅግ ለአይን በሚስቡና በሚማርኩ
ሰማይና ምድር ከተፈጠረ ጀምሮ የሰው እጅ ያልነካቸው በሚመስሉ ጥቅጥቅ ባሉ ደኖች ለዘመናት ተደብቆ የኖረና በቅርቡ የተገኘ ዋሻ ነው፡፡ ዋሻውን ለየት የሚያደርገው ከዋሻው አናት ላይ ቁልቁል 30 ሜትር
ላይ እየተወረወረ ዋሻው ስር የሚፈሰው ፏፏቴ በውበት ላይ ውበትን አጎናጽፎታል፤ የዋሻው መግቢያ ከፍታው ከወለሉ እስከ ጣሪያ
15 ሜትር ሲሆን ርዝመቱ ከመግቢያው እስከ ጫፍ 50 ሜትር እንደሚሆን ይገመታል፡፡
የደንቢ ፏፏቴና ግድብ
ይህ መስህብ በደ/ቤንች ወረዳ በቂጤ
አካባቢ በፋኒቃ ቀበሌ የሚገኝ ሲሆን ከሚዛን ከተማ በ19 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ የደንቢ ግድብ ለሃይል ማመንጫነት ታስቦ
በአካባቢ ያሉት ጉብታዎች በመጠቀም የተሰራ ግድብ ሲሆን ከ3 ሔክታር በላይ ስፋት ሲኖረው ፏፏቴው ደግሞ 14 ሜትር ከፍታ እንዳለው
ይገመታል፡፡ ፏፏቴው ተወርውሮ መሬት ላይ ሲያርፍ የሚፈጥረው ጢስ መሰል እንፋሎት አካባቢውን የጥጥ ባዘቶ ሲያስመስለው ማየት እጅግ
ያስደስታል፡፡ መስህቡ ካለው እምቅ የቱሪዝም ሀብትና ከቅርበቱ አንጻር ቢለማ ለሎጅና ኢኮ-ቱሪዝም ምቹ በመሆኑ የጎብኝውን ቀልብ
እንደሚስብ ይታመናል፡፡
ሼይ ቤንች እና መስህቦቿ
የሼይ ቤንች ወረዳ በቤንች ማጂ
ዞን ከሚገኙ 10 ወረዳዎች ውስጥ አንዷ ስትሆን ከዲስ አበባ
561 ኪ/ሜ ከክልሉ ርዕስ ከተማ ሀዋሳ 860 ከኪሎ ሜትር ከዞኑ
ዋና ከተማ ሚዛን አማን ደግሞ በ51 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ ወረዳዋ በ20 የገጠር ቀበሌና በ1 ማዘጋጃ ቤት የተዋቀረች
ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ወደ 131,000 ህዝብ እንደሚኖርባት ይገመታል፡፡
የአየር ንብረቷም በአብዛኛው ወይናደጋ
በመሆኑ ለኑሮ እጅግ ተመራጭና ተስማሚ አድርጓታል፡፡ ይህንን ተከትሎም የተለያዩ ሰብሎችና ቅመማ ቅመሞች ይመረቱባታል በዋኝነት በቆሎ፣
ጤፍ፣ ስንዴ፣ ማሽላና በቄላ ከቅመማ ቅመም ደግሞ በአብዛኛው በኮረሪማ ምረት ትታወቃለች፡፡ የእንሰሳት ሀብቷም ቢሆን ቀላል አይደለም፡፡
ወረዳዋ ካላት ልምላሜ አንጻር ለኢንቨስትመንት ምቹ በመሆኗ ሊለሙ የሚችሉ ቦታዎች በገጠርም ሆነ በከተማ ተለይተው የተቀመጡ በመሆናቸው
ልማታዊ ባለሃብቶችን በመጠባበቅ ላይ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ወረዳዋ ለጭስ አልባው ኢንዱስትሪ (Eco-tourism) አመች በመሆኗ
ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራበት ይገባል በወረዳው ከሚገኙ የመስህብ ሀብቶች መካከልም የተወሰኑትን እንቃኛለን፤
ቀይ ውሃ ፏፏቴ
የቀይ ውሃ ፏፏቴ ከወረዳው ከተማ
5 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከምትገኘው ዚያግን ቀበሌ በመኪና ከተጓዙ በኃላ በእግር 30 ደቂቃ ይንቀሳቀሳሉ፤ ከስያሜው አንጻር ፏፏቴው
ቀይ ሳይሆን መነሻው ከጨፌ ውስጥ በመሆኑ በአብዛኛው የጨፌ ውኃ ቀይ የመምሰል ባህሪ ስላለው እንደሆነ ይነገራል፡፡ ይኽው የቀይ
ውኃ ፏፏቴ ሁሉት በሚባል ቦታ ላይ የሚገኝ ሲሆን የመጀመሪያው ከዋናው መንገድ 30 ደቂቃ የእግር ጉዞ በኃላ የሚያገኙሰት ሲሆን
ፀሐይ ሳይነካዎት በተፈጥሮ ደኖች ውስጥ በአዕዋፍ ዝማሬ ታጅበው በመጓዝ ያገኙታል፡፡
መንትዮች የቀይ ውኃ ፏፏቴዎች
ሌላ የቀይ ውኃ ፏፏቴ ከመጀመሪያው
ፏፏቴ በእግር 30 ደቂቃ ያክል ተጉዘው ይገኙታል፡፡ በግምት የ40 ሜትር ርዝመትና የ5 ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን በሁለት አቅጣጫ
የሚፈሰው የፏፏቴ ውኃ ትልቅ ሽለቆ በመፍጠር መንትዮቹ ፏፏቴዎችን አንድ አድርጎ ይነጉዳል፡፡ በተለይ በክረምት ወራት ውኃው ሲሞላ
በከፍተኛ ፍጥነት እየተንደረደሩ ሲወረዱ አካባቢውን የጥጥ ባዘቶ ያስመስሉታል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በዘንድሮ አመት በወረዳው
10 ሔክታር የተፈጥሮ ደን የተከለለ በመሆኑ አካባቢውን ውብና ማራኪ ያደርገዋል፡፡
ሰው ሰራሽ ፏፏቴ
ከፏፏቴዎች ሳንወጣ በቻይናውያን
መንገድ ስራ ዚያግን ቀበሌ ውስጥ ከመንገድ 5 ደቂቃ ወደ ውስጥ ገባ ብሎ ለመንገድ ስራው ከፍተኛ የሆነ የድንጋይ ምርት ካወጡ በኋላ
ድንጋይ የወጣበት አካባቢ ከ600 ካ/ሜ በላይ የሚሆን የዳንጋይ አጥር /ካብ/ በመፈጠሩ እርሱን ተከትሎ ከመንገድ ድልድይ ሰር በሚመጣው
ወንዝ አማካኝነት በግምት ከ15-20 ሜትር ርዝመት ያለው የውኃ ፏፏቴ ተፈጥሮአል፡፡ ቦታው ከከተማው ቅርበት አንጻር ቢለማ ጥሩ
የመዝናኛ ስፍራ ይወጣዋል፡፡
ሶያ ኩሻ ዋሻ
ዋሻው የሚገኘው በማዝ ቀበሌ ውስጥ
ሲሆን ከወረዳው 32 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ከወረዳው በመኪና የሚጓዙ ሲሆን ከቀበሌዋ ደግሞ በእግር 30 ደቂቃ ይፈጃል፡፡
መንገዱም በእግር አስቸጋሪ አለመሆኑ ለጎብኚዎች ሞቹ አድርጎታል፡፡ የዋሻው ርዝመት በግምት 50 ሜትር ከፍታው ደግሞ 9 ሜትር ሲሆን
እንደ ምሰሶ መግቢያው ላይ የቆመው ጥርብ ድንጋይ ሁለት በር ፈጥሯል፡፡ በውስጡም በርካታ የሌሊት ወፎች፣ ጃርት፣ ጎሽ እንደሚኖሩ
ይነገራል፡፡ ዋሻውን ቀደም ሲል ለጠላት መከላከያነት እንደሚጠቀሙበት ከዚህም በተጨማሪ ሰዎች እርሻ ስራ ላይ ውለው ሲደክማቸው የሚያርፉበትና
እህል ውሃ የሚቀማምሱበት እንደሆነ ይነገራል፡፡ በዋሻው ውስጥ ከአለቶች የሚወጣ እጅግ የላመ ጨው መሰል ነገር ሲኖር ከብቶች ይልሱታል፡፡
No comments:
Post a Comment