የሜኤኒት ጎልዲያ መስህቦች
በቤንች ማጂ ዞን ከሚገኙ 10 ወረዳዎች አንዱ የሆነው የሜኤኒት ጎልዲያ
ወረዳ ርእሰ ከተማ ባቹማ ትባላለች፡፡ ባቹማ ከአዲስ አበባ በ591 ኪሎ ሜትር ከሚዛን ደግሞ በ87 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ስትገኝ
ወረዳው የሜኤኒት ብሔረሰብ መገኛም ነው፡፡
የባንዲሊ የተፈጥሮ ዋሻ
በቤንች ማጂ ዞን የቱሪስቶችን ቀልብ
የሚስቡ በርካታ ተፈጥሮአዊና ባህላዊ መስህቦች ይገኛሉ፡፡ በዞኑ በየጊዜው አዳዲስ የቱሪስት መስህቦችን ማግኘት የተለመደ ክስተት
ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በመኤኒት ጎልዲያ ወረዳ መኖሩ የማይታወቅ በይዘቱና በመስህብነቱ ወደር የማይገኝለት የተፈጥሮ ዋሻ በአካባቢ
ነዋሪዎች ጥቆማ ተገኝቷል፡፡ ዋሻውን የአካባቢ ነዋሪዎች ቀፎ ለመስቀልና የጫካ ማር ከዱር ለመቁረጥ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት እንዳገኙት
ይናገራሉ፡፡ በመሆኑም የተፈጥሮ መስህቡን በማጥናት በዞኑ የተፈጥሮ መስህቦች ዝርዝር ውስጥ ሊካተት ችሏል፡፡
ይህ የተፈጥሮ ዋሻ መጠሪያ ስሙ
ባዲሊ ሲባል በብሔረሰቡ ቋንቋ ጎንና ጎኑ የግማሽ ጨረቃ ቅርጽ ያለው ነጭ ደመና ማለት ነው፡፡ ትርጉሙም የዋሻው መግቢያ በር የግማሽ
ጨረቃ ቅርጽ ያለውና የፏፏቴው ውሃ ተወርውሮ በሚፈጥረው ነጭ ጉም እና ትዕይንት የተነሳ የተሰጠው ስያሜ እንደሆነ ይነገራል፡፡ የባዲሊ
ዋሻ በሜኤኒቲ ጎልድያ ወረዳ በኩሻንታና ሻርማ ቀበሌዎች ድንበር ላይ የሚገኝ ሲሆን በስተምስራቅ አቅጣጫ ከከፋ ዞን ጎባ ጫራ ወረዳ
ጋር ይወስናል፡፡ መስህቡ ከወረዳው ርዕስ ከተማ ከባቹማ በ6፡00 ሰዓት ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ወደ ዋሻ የሚያስገባ የመኪና መንገድ
ስለሌለው በእግር አልያማ በጋማ ከብት መሄድ ግድ ይላል፡፡ በመስህቡ ቅርብ ርቀት ላይ የተጀመረው ሰፊ የእርሻ ኢንቨስትመንት ወደ
መስህቡ የሚወስደውን ርቀት እንደሚቀንሰው ይገመታል፡፡
የባዲሊ ዋሻ መግቢያ በሩ ጠበብ
ብሎ ውስጡ ግን በጣም ሰፊ በመሆኑ ከአንድ ትልቅ አዳራሽ አያንስም
ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ዋሻው ከ200 ሰዎች በላይ የመያዝ አቅም እንዳለው ይገመታል፡፡ በዋሻው በስተጀርባ በኩል ሰፊ አፍ ሲኖረው
የጎኑ ስፋት 30ሜትር የከፍታ ርዝመቱ ደግሞ 50 ሜትር እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይህን ዋሻ ከሌሎች ዋሻዎች ለየት የሚያደርጉት
ነገሮች ከዋሻው በስተጀርባ በኩል የሚፈስ ትልቅ ወራጅ ወንዝ ሲኖረው በዋሻው አጠገብ አነስተኛ ከፍታ ያለው ፏፏቴ ይፈጥራል፡፡ በፏፏቴው
የወረደው ውኃ ዋሻው ስር ጠባብ ሀይቅ መሰል ውሀ በመፍጠር ዋሻውን ውብና ማራኪ አድርጎታል፡፡ በዋሻው ዙሪያና አናት ላይ የበቀሉ
ዕድሜ ጠገብ ጥቅጥቅ ያሉ ዛፎች ለዋሻው ግርማ ሞገስ አጎናጽፈውታል፡፡ ሌላው የሚያስደምመው ነገር ደግሞ ከዋሻው ገደል ስር ከፍተኛ
የንብ መንጋ በመኖሩ አንዳንድ የአካባቢው ነዋሪዎች ወደ ስፍራው በመሔድ
ከጠንካራ ሀረግ በተሰራ ካንታ ውስጥ ሆነው በረጅም ወፍራም የሀረግ ገመድ ተንጠልጥለው ጋራው ስር በመውረድ ማር ቆርጠው እንደሚጠቀሙበት
ይገልጻሉ፡፡
የባዲሊ ዋሻና አካባቢው ከሰዎችና
ከቤት እንሰሳት መኖሪያ በጣም ርቆ ስለሚገኝ ከንኪኪ ነጻ ነው፡፡ በስፍራው ከአዕዋፋት ዝማሬና የዱር እንሰሳት ጩኸት ውጭ ምንም
የሚሰማ ነገር የለም፡፡ በዚህ የተነሳ በስፍራው የተለያዩ የዱር እንሰሳት እንደ ነብር፤ አንበሳ፤ ጎሽ፤ ድፈርሳ፤ አሳማ ድኩላ ወዘተ
ከዋሻው ዝቅ ብሎ በሚገኘው ሀይቅ መስል ውኃ ውስጥ አዞና አርጃኖ እንደሚገኙ ይገልፃል፡፡
ዳል ፏፏቴ
ይህ ፏፏቴ ከባቹማ ከተማ ወደ ጋችት ቀበሌ በሚወስደው መንገድ ላይ
የ3 ሰዓት የእግር ጉዞ ርቀት ላይ ተራማጅ ቀበሌ ይገኛል፡፡ የፏፏቴው ከፍታ በግምት 62 ሜትር ሲሆን ፏፏቴው ከከፍተኛ ቦታ ቁልቁል
እየተወረወረ ከስር ካለው ጥልቅ ሸለቆ ውስጥ ይፈሳል፡፡ የፏፏቴው አካባቢ መስክ በአደይ አበባ ያጌጠና ያሸበረቀ ሲሆን አፋፉ ላይ
ቆሞ ፏፏቴው የሚፈጥረውን ትርኢት ማየት በጣም ያስደስታል፡፡
ይጢ ፏፏቴ፡-
ይህ ፏፏቴ ከዳል ፏፏቴ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን ከረጅም ተራራ
አናት ላይ ቁልቁል እየተንደረደረ ሸለቆ ውስጥ ይገባና ከዳል ፏፏቴ ውኃ ጋር ተቀላቅለው ይጓዛሉ፡፡ የፏፏቴው ከፍታ 75 ሜትር ሲገመት
መንታ መሆናቸው ለተመልካች የተለየ ስሜት ይፈጥራል፡፡
ኩይ ፍል ውሐ፡-
ይህ ፍል ውኃ በሜኤኒት ጎልዲያ ወረዳ በኩበት ወረዳ ቀበሌ የሚገኝ
ቢሆንም ወደ ፍል ውሐው ለመሄድ 2 ሰዓት ድረስ ያስኬዳል፡፡ ይህ ፍል ውኃ በሁለት ወረዳ ድንበር ላይ በሚገኘው አልሙ ወንዝ አጠገብ
መገኘቱ ይበልጥ ተፈጥሮን ለሚያደንቁ ተጨማሪ አማራጭ ይሆናል፡፡ በተጨማሪም በፍል ውኃው ለመታጠብ የሚያስችል አሸንዳ ያለው መሆኑ
እንዲሁም የአካባቢው ተፈጥሮአዊ መልከአ ምድር በስፍራው የሚገኙት እንደ ጎሽ፣ ዝንጀሮ፣ ጉሬዛና ዱር አሳማ የመሳሰሉት እንስሳት
ከፍል ውኃው ጠበልነት ጋር ተዳምሮ ለጎብኚ ተመራጭ ያደርጉታል፡፡
ኢንቨስትመንትና ቤንች ማጂ
ለቋሚ እና ጊዜያዊ ሰብሎች፣ ለፍራፍሬ ልማት፣ ለጎማ ዛፍና ፓልም ዛፍ፣
ለከበሩ ማእድናትና ሌሎች ከርሰ ምድር ሀብት የወርቅ፣ የማዕድን ውሃ፣ እና ሌሎችም ዘርፈ ብዙ ሃብቶች እና የኢንቨስትመንት አማራጮች
የሚገኙበት ቤንች ማጂ ዞን ባለፉት አስራ አምስት ዓመታት በተለያየ ዘርፍ መዕዋለ ንዋያቸውን ያፈሰሱና ወደ ልማት የገቡ ባለሃብቶች
በርካታ ናቸው፡፡
በእርሻ መስክ ከ72 በላይ በአገልግሎት መስጫ ተቋማት 30 በአግሮ
ኢንዱስትሪ 35 ባለሃብቶች ከ63962 ሄክታር በላይ የሆነ መሬት በመረከብ ከ4.5 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል በማፍሰስ ከ25 ሺ
በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል የፈጠረ የልማት እንቅስቃሴ ላይ ለመሰማራት ችለዋል፡፡
ዞኑ ካለው ከፍተኛ አቅም በየጊዜው እየተስፋፋ ከመጣው መሰረተ ልማት
እና ከምንጊዜውም በላይ ትኩረት እየተቸረው ለመጣው አረንጓዴ ኢንቨስትመንት ካለው ምቹ ሁኔታ አኳያ የቀጣዩ ጊዜ የልማት ቀጠና እንደሚሆን
አያጠራጥርም በዚህም በእርሻው ክፍለ ኢኮኖሚ ንብ እርባታና ፕሮሰሲንግ፣ በእንስሳት ማደለብ፣ በወተትና ወተት ተዋጽኦ፣ በዶሮ እርባታና
ቅመማ ቅመም፣ በፍራፍሬና ጃትሮፋ፣ በከተማ ግብርና እና በሌሎች መስኮች መሳተፍ ለሚፈልጉ ባለሃብቶች ወደ 35000 ሄክታር የሚጠጋ
መሬት የተዘጋጀ ሲሆን ለልማታዊ ባለሃብቶች ትኩረት የሚሰጠው ዞናችን ቀልጣፋ አገልግሎት የሚያገኙበት በመሆኑ ኑና ቤንች ማጂን አልሙ
ሲል ዞኑ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
No comments:
Post a Comment