መስቀል በአዲግራት
መስቀል በአዲግራት |
መስቀል በሃገራችን በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት አንዱ ነው፡፡ በተለይም የደመራ
በዓል ከፌስቲቫል ቱሪዝም ሀብታችን ውስጥ ግንባር ቀደሙን ቦታ ይይዛል፡፡ ይህንን በዓል የሰው ልጆች ሁሉ እሴት ለማድረግም ጥረቶች
ተጀምረዋል፡፡ መስቀልን በዩኔስኮ ለመመዝገብ በቅቷል፡፡
መስቀል እንደ የኢትዮጵያውያን እሴትና ባህል ከዳር ዳር የሚከበር ከአደይ
ጋር አብሮ የሚፈካ፣ ከዘመን ጋር የሚጠባ በዓል በመሆኑ ይበልጥ ደማቅ እንዲሆን አድርገዋለል፡፡
በድንቅ እሴት የተሞላውና ብዙ ሳይነገርለት የኖረው የምስራቃዊ ትግራይ ዞን
የመስቀል በዓል አንዴ ሌላ የባህል ሃብት መስህባችን ነው፡፡
አዲግራት የዞኑ መዲና ናት፡፡ አዲግራት ለመስቀል የተመለከታት ትዝታውን ዘለዓለም
ተሸክሞ ይኖራል፡፡ ፌሽታው በባህል የታጀበ ነው ሆታው ሁሌም ከመንፈስ ተቆራኝቶ ይኖራል፡፡
በአዲግራት ዙሪያ ያሉ ተራሮች በእፅዋት ያጌጣሉ፤ ምድር አረንጓዴ ኩታ የምትለብሰበት
ወቅት ነው፡፡ በየቤቱ ደግሞ ደስታ አለ መስቀል በናፍቆት ሲጠብቅ የኖረ መንፈስ ያወደው ደስታ! በትግራይ ምስራቃዊ ዞን ተወላጅ
! ለመስቀል ቀዬው መግባትና በዓሉን ከአብሮ አደጎቹ ጋር ማሳለፍ የተለመደ ነው፡፡
በገጠር ሳይቀር መስከረም እንደገባ መስቀል ሳምንት ሲቀረው ዝግጅቱ ይጦፍል
”ዓኸይ ዓኾኾይ” እየተባለ የወይራ እንጨት ተቀጣጥሎ የወተት ማለቢያ እቃዎች ሳይቀር ይታጠናሉ፡፡ ወተትና የወተት ተዋጽኦ በስፋትና
በአይነት የሚዘጋጁበት የመስቀል በዓል በጉጉት ሲጠበቅ የሚኖር፤ ቤተሰብ
ለቤተሰብ ፍቅርን የሚገላለፅበት በዓል ነው፡፡
በገጠሩ አካባቢ በዋዜማ ማለትም መስከረም 16 ቀን ወጣቶች ቅቤ ይቀባሉ፤
ወተትና ዳቦ ይሰንቁና ከፍቶቻቸውን እየነዱ ወደ በረሃ ይወርዳሉ፡፡ የሚመለሱት ምሽት ላይ ነው፡፡ በዓሉ መድመቅም የሚጀምረው ይሄኔ ነው፡፡ በረሃ የዋሉት ወጣቶች ለደመራ የሚሆን
እንጨት ስብስበው ሆ! እያሉ ይመለሳሉ! መንደሮች በችቦና በተስፋ ብርሃንን ይሞላሉ… ምሽቱ በሆታና በችቦ እሳት ይፈካል በዓመት
አንዴ ተመሳሳይ በሆነ ስሜት በተመሳሳይ እሴት ይደምቃል፡፡ በእንግድነት እዚህ መሃል ለተገኘ! እንዴት ስለ ትግራይ መስቀል ሳልሰማ
ኖርኩ ብሎ ይገረማል የበለጠ የሚገረመው ግን በሚያየው የባህል እሴት ነው፡፡ ከየቤቱ በተሰበሰቡ እንጨቶች የሚደመረው ደመራ በልጆች
የሆያ ሆዮ ዜማ ታጅቦ ይለኩሳል፡፡
ደመረው የእሳት ብርሃን ሳይተፋ ካህናት ፀሎት ያደርሳል፡፡ “መስቀል አብረሃ”
እያሉ ያዜማሉ በከዋክብት አብርቷል፤ ሰማይን አስጊጧል፤
ሆያየ ሆየ! ሆየ እያለ እንደ ካህናቱ ሁሉ ህዝቡም በደመራው አውድ ያዜማል
ሴቶች እልል ይላሉ…
አዲግራት የዚህ እሴት ማዕከላዊ ከተማ ናት፤ መስከረም 16 አዲግራት በፅሁፍ
የማይገለፅ ሃሴትን ትሞላለች! ሁሉም ሰው ላይ ሁሉም ቦታ ከሁሉም ሰው በፌት ደስታ ይጨለፋል፡፡
ወንድ ሴቱ አለባበሱ የባህል ነው፡፡ አንዴ አብሮ የታደመ እንግዳ አይኑን
በጨፈነ ቁጥር ሁሌም ይህንን ክስተት ይስታውሳል፤ ከተማ በደስታና እና በባህል ወግ ማዕከል ስትጥለቀለቅ ለማየት መስቀልን ከአዲግራት
ጋር ማገጣጠም ነው፡፡
ፈጣን የንግድ እንቅስቃሴ ካለባቸውና ለኢንቨስትመንት አዋጪ ከሚባሉ የሃገራችን
ከተሞች አንዷ የሆነች አዲግራት ይህንን መሰል ባህል ጠብቆ በማኖርም ረገድ የእሴት ማዕከል በመሆኗ ልትወደስ ይገባታል፡፡
ምሽት…የአዲግራት ጉዳናዎች ተለኮሶ ችቦ ይዘው ሰው እግር ስር ለመጣል በሚርመሰመሱ
ወጣቶችና ህፃናት ይሞላሉ፡፡
እግሩ ስር ችቦ የተጣለበት ሰው ችቦውን በመሻገር ከዘመን ዘመን መሻገሩን
በምሳሌ ገልፆ ችቦውን እግሩ ስር ለጣለው ሽልማት ይሰጣል፡፡
ከአዲግራት አናት ላይ ባለው ተራራ ምድሪቱ ስትጨልም የችቦ ብርሃን ይዘው
ሆ! እያሉ የሚያልፍ ሰልፍኞች ሌላ ብርሃን ይፈነጥቃሉ! ተስፋን የሰነቀ አዲስን ዓመት የሚያበስር ብርሃን!
በመስቀል እሳት በጋለ ድንጋይ ላይ የፍየል ስጋ ይጠበሳል፡፡ ያንን በጋራ
በልቶ በጋራ ሆ ይባላል፡፡ አባወራው ከመስሎችቹ ተለይቶ ወደ ቤቱም ሲገባ መብላቱ መጠጣቱ መጫወቱ ከቤተሰቡ ጋር ይቀጥላል፡፡
“ጥሕሎ” ባህላዊ ምግብ ነው፡፡ አመጋገቡ፣ መስተንግዶ፣ህብረቱና ጣዕሙ በአንድ
ላይ ሆነው የላቀ ትርጉም አስጥተውታል፡፡ ከማር ጠጅ እያወራረዱ ጥሕሎን በህብረት መመገብ ቆይታን አይረሴ ያደርገዋል የአዲግራት
ደመራ መስከረም 17 ቀን ጠዋት ነው የሚለኩሰው፡፡ ህዝቡ ሁሉ ወደ ስታዲየሙ ወፍ ሲጮህ ጀምሮ ይከተታል፡፡ የባል ልብሱን ለብሶ
ሐገርኛ ሆኖ…የወጣቶች አለባበስ እንኳን በራሱ ቅርስ ነው፡፡ የአዲግራት ወጣቶች መስቀልን በሃገር ወግ ማክበርን ተክነውታል፡፡
በብርሃን ደመራው ይለኮሳል! ከደመራው ግዝፈት የተነሳ ግን ፀሐይ የምትለግሰውን
ብርሃን የሚገዳደር ወጋገን ፍንትው ይላል፡፡
የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ይዘምራሉ፣ ካህናት መስቀል አብረሃ ይላሉ…
ምትክ የሌለው የሴቶች የእልልታ ድምፅ አዲግራት ያሰክራታል፡፡ የተለኮሰው ደመራ አመድ ሆኖ ትርኳሹ ለበረከት እስኪነሳ ህዝቡ ደስታውን
እየገለፀ ይቆያል፡፡
ሁሉም ሰው በዓል መስቀል…ሳይይጠግብ ያልፋል! እንደተናፈቀ ይመጣል…መስቀል
በአዲግራት
No comments:
Post a Comment