Thursday, August 9, 2012


የሲዳማ ዘመን መለወጫ /ፍቼ/ በአል አከባበር

ከይረጋዓለም ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር


ፍቼ በዓል በሲዳማ
ፎቶ ከሲዳማ ባ/ቱ/መ/ኮ/መምሪያ

“ፍቼ” በሲዳማ ባህል ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ የቆየ የዘመን መለወጫ በአል ነው፡፡ በአሉ ከሁለት ሳምንት ላላነሰ ጊዜ በድምቀት የሚከበር ሲሆን አከባበሩም ቅደም ተከተላዊ ሂደትና በደረጃ እየሰፋ የሚሄድ የጋራ የአከባበር አድምታ ያለው ነው፡፡ ስለሆነም ፍቼ በቤተሰብ ወይም በጎረቤት ደረጃ ተሰባስቦ በማክበር የሚያበቃ ሳይሆን ከዚህም በሰፋ መልኩ በባህላዊ አደባባይ /ጉዱማሌ/ በጋራ በድምቀት የማክበር ሂደትን ያካትታል፡፡ ለአከባበሩ እያንዳንዱ ቤተሰብ በቅድሚያ እንደ አቅሙ ቅድመ ዝግጅት ያደርጋል፡፡ ከዚሁ አንጻር የቤቱ እመቤት ለበአሉ ቅቤ ታጠራቅማለች ወተት በታጠነ ማለፊያ “ቁሹና” /የወተት እቃ/ ታከማቻለች የእንሰት ውጤት የሆነውን ቆጮ ለበአሉ በሚሆን መጠንና ጥራት ከወዲሁ ታሰናዳለች፡፡


አባወራው በፍቼ ማግስት /በጫምበላላ/ እለት ለከብቱ የሚያበላውን ቦሌ ያዘጋጃል፡፡ ልጃገረዶች ለበአሉ መዋቢያ ለእግሮቻቸውና ለእጆቻቸው ጣቶች ቀለበት፣ ለፀጉራቸው መስሪያ “ሄቆ” /የተለያዩ ቀለማት ያሉት የቱባ ክር/፣ ጨሌ፣ ለአንገታቸው ቡሪቻና ዶቃ የጌጥ አይነት ለጸጉራቸው ማሸሚያ ግንባራቸው ላይ የሚያስሩትን በእራፊ ጨርቅ ላይ ደርድረው የሚሰፉትን ኢልካ /አዝራር/ ወዘተ የመሳሰለውን ያስገዛሉ እግራቸውና እጃቸው ላይ የሚቀቡትን እንሶስላ ያዘጋጃሉ፡፡

 

ፍቼ/Fichchaa/
የሲዳማ ሸንጎ
ፎቶ ከሲዳማ ባ/ቱ/መ/ኮ/መምሪያ

የፍቼ ዕለተ በዕለተ ቃዋዶ በአሉ መከበር የሚጀምረው ከአመሻሽ ጀምሮ ነው፡፡ ለዚህም በቅቤ የራሰ “ቡሪሳሜ” ከቆጮ የተሰራ ባህላዊ ምግብ “በሻፌታ” /ከሸክላ በተሰራ ባህላዊ ገበታ/ ቀርቦ በወተት በጋራ የመመገብ ሥርዓት የሚካዳሄድ ሲሆን አመጋገቡ የሚጀምረው በአካባቢ ከሚገኝ አንጋፋ ወይም ጪሜሳ /ብቁ አረጋዊ ቤት/ በመገኘት ገበታው ከቀረበ በኋላ ለቡራኬው ሁሉም እጁን በገበታው ትይዩ በመዘርጋት “ፍቼ ከዘመን ዘመን አድርሽን” በማለት አንጋፋው የሚሰነዝረውን ቡራኬ ቃል በጋራ በማስተጋባት አመጋገቡ ይጀምራል፡፡ ለመመገቢያ በቅድሚያ ለሁሉም በእሳት ሙቀት ተለብልቦ የለሰለሰ ኮባ ስለሚታደል አንጋፋው በኮባው ከገበታው በመጨበጥ ከጀመረ በኋላ በጋራ የመመገቡ ሂደት ይጀምራል፡፡ በፍቼ እለት በየቤቱ የሚቀርበው ገበታ ውስጥ ሥጋ አይካተትም፡፡ የዚህ አይነተኛው ምክንያት ከብቱም በሰላም ከዘመን ዘመን መሸጋገር ስላለበትና ሲዳማ ለከብት ከፍተኛ ግምት ያለው በመሆኑ ነው፡፡



ቀደም ሲል ታርዶ ሲበላ የተረፈ ሥጋ እቤት ውስጥ ካለ በእለቱ ሥጋው ከቤት ውጪ እንያዲያድር ይደረጋል፡፡ አባወራ /የቤቱ ባለቤት /በፍቼ እለት ከቤቱና ከቤተሰቡ ተለይቶ ሌላጋ አያድርም፡፡ በዚህ እለት በየደጁ ከእርጥብ እንጨት “ሁሉቃ” የተሰኘ መሹለኪያ ተዘጋጅቶ አስቀድሞ አባወራው በሁሉቃው ውስጥ ከሾለከ በኋላ ቤተሰቡንና ከብቱን ያሾልካል ይህም በሰላም ከዘመን ዘመን የመሸጋገር ተምሳሌት ነው፡፡



የጨንበላላ /የፍቼ ማግስት/ አከባበር

“ጫንበላላ” በፍቼ ማግስት በእለተ ቃዋለንካ  የሚከበር ሲሆን የፍቼ እለት በጋራ በተበላበት “ሻፌታ” /ባህላዊ ገበታ/ ውሃ ተሞልቶ ጠዋት ላይ አባወራውና ቤተሰቡ በውሃው ፊታቸውን በማስነካት እና ከዚሁ ጋር የቀረበውን ቅቤ አባወራው እየቆነጠረ የራሱን እና የቤተሰቡን አናት በማስነካት ወደ አዲሱ ዘመን የመሸጋገር ተምሳሌት ይከናወናል፡፡ የ“ጨንበላላ” እለት መሬት የማረስ እንጨት የመስበር የመሳሰለውን ተግባር ስለማይከናወን ለማገዶም ቢሆን አስፈላጊው እንጨት አስቀድሞ ይዘጋጃል፡፡ በዕለቱ አባወራው ከብቶቹን ማለፊያ “ካሎ” /የግጦሽ ሳር/ ውስጥ አሰማርቶ ለከብቱ ቦሌ ነስንሶ እያበላ ከብቱን አጥግቦ ያውላል፡፡ በዚህ ዕለት ልጆች ተሰባስበው በየቤቱ በመሄድ “አይዴ ጨምባላላ” እንኳን አደረሳችሁ ሲሉ የቤቱ ባለቤቶች ምላሹን “ኢሌ ኢሌ” ከዘመን ዘመን ያድርሳችሁ በማለት ልጆቹን አጥግበው ያበሏቸዋል፡፡ አናታቸውን ቅቤ ይቀቧቸዋል፡፡ በዚህ ዕለት ልጆችንም ሆነ ከብትን በአርጩሜ መምታት ነውርና አይደረጌ ነው፡፡



ፍቼ ፋሎ

“ፍቼ ፋሎ” የፍቼን በዓል በጋራ በባህላዊ አደባባይ በድምቀት የማክበር ሥነ-ሥርዓት ነው፡፡ ስለሆነም በአመዛኙ የፍቼ ዕለተ ቀን በተከበረ በሶስተኛው ቀን አሊያም አንደአካባቢው በተመረጡ ቀጣይ ቀናት “ፈቺ ፋሎ” ወይም /ሻሻጋ/ በባህላዊ አደባባይ በጋራ ይከበራል፡፡አደባባዩ “ጉዱማሌ” ይባላል፡፡ “ጉዱማሌ” የፍቼ በአል በጋራ የሚከበርበትና እንዲሁም በሌላ ጊዜ የጎሳ መሪዎችና “ጭሜሳዎች” /ብቁ አረጋውያን/ ልዩ ልዩ ባህላዊ ስርዓት የሚያከናውኑበት የተከበረ ባህላዊ ስፍራ ነው፡፡ ህብረተሰብ በአሉን ለማክበር በጎሳ በጎሳ በመሆን በተለያየ ባህላዊ ጭፈራና ባህላዊ አልባሳት አጊጠው ወደ “ጉዱማሌ” ይጓዛሉ፡፡ ሁሉም በጋራ በየጎሳው ወደ “ጉዱማሌ” ከገቡ በኋላ የባህላዊው ሃይማኖት አባቶችና የጎሳ መሪዎች እንደ ማህበራዊ ደረጃቸው በየተራ ንግግር ያደርጋሉ፣ ይመርቃሉ፣ ባሮጌው ዘመንና በአዲሱ ዘመን ላይ ያተኮሩ መልእክቶች ያስተላልፋሉ፡፡ በጎው እንዲጎለብት አስከፊው እንዳይደገም ምክር አዘል መልዕክት ያስተላልፋሉ፤ ዘመኑ የሰላም፣ የብልጽግና የልማት ይሆን ዘንድ ቃል ቡራኬ ያደርሳሉ፡፡

(የሲዳማ ዞን ማስታወቂያና ባህል መምሪያ በ2001 ዓ.ም ካሳተመው ፍቼ መጽሄት የተወሰደ፡፡)

2 comments: