Tuesday, May 19, 2015



የምሁር አክሊል ወረዳ
ፎቶ፡-በገዝ ወንዝ
በጉራጌ ዞን ከሚገኙት ወረዳዎች አንዱ ሲሆን በ30 ቀበሌዎች እና በ1 የከተማ አስተዳደር የተዋቀረ ነው፡፡ ወረዳው በሰሜን ከኪር ገደባኖ ወረዳ፣ በምስራቅ መስቃን ወረዳ፣ በደቡብ እዣወረዳ እና በምዕራብ ቀቤና ወረዳዎች ያዋስኑታል፡፡ የወረዳው የህዝብ ብዛት 107.224 እንደደረሰ ከሥነ ህዝብ የተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ማህበረሰቡ በአብዛኛው የሚተዳደረው  በእንስሳት እርባታና በእርሻ ነው፡፡


Saturday, April 25, 2015



ባሌ ዞን
የባሌ ዞን በኦሮምያ ክልል ከሚገኙ ዞኖች አንዱ ሲሆን በቆዳ ስፋቱም ሁለተኛው  ነው፤ በስተምስራቅ የሶማሊያ ክልል፣ በሰሜናዊ ምስራቅ ምስራቅ ሐረርጌ፣ በሰሜን ምዕራብ ሐረርጌና አርሲ ዞን፣ በምዕራብ ምዕራብ አርሲ እና በደቡብ ጉጂ ዞን ያዋስኑታል፡፡ ዞኑ 14.93 በመቶ በደጋ፣ 21.54 በመቶ በወይናደጋ እና 63.53 በመቶ በቆላ የአየር ንብረት የተከፋፈለ ነው፡፡ መልከዓ ምድራዊ አቀማመጡም 55.89 በመቶ ሜዳማ፣ 30.7 በመቶ ወጣ ገባማ፣ 12.14 በመቶ ተራራማ እና ቀሪው 0.4 በመቶ ሸለቆማ ነው፡፡ በሀገራችን የቱሪዝም መስህቦች አንጋፋውን ስፍራ ከሚይዙ አካባቢዎች አንዱ የሆነው የባሌ ዞን እጅግ በርካታ የሆኑ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችን የታደለ ምድር ነው፡፡ ጥቂቶችን በዚህ ዕትም እንዳስሳለን፡፡


Friday, April 24, 2015



አርኪዎሎጂ
የሰው ዘር መገኛነታችንን ዳግም ያረጋገጠው ግኝት
ኢትዮጵያ ቀደምት የሰው ዘር መገኛ መሆኗን ያረጋገጡ የተለያዩ ግኝቶች በተለያዩ ጊዜያት ተገኝተዋል፡፡ የሉሲ(ድንቅነሽ) እ.ኤ.አ በ1974 ዓ.ም.፣ አርዲ እ.ኤ.አ 2009 ዓ.ም. እንዲሁም ሆሞሳፒያን ኢዳልቱ እ.ኤ.አ 1997 ዓ.ም. ከተገኙት ግኝቶቹ በዋናነት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ፋና ወጊነታችንን የሚያጠናክሩ ግኝቶች እየተገኙ ቢሆንም የመጀመሪያውን የሆሞ የቅድመ ሰው ዘር እድሜ ይታመንበት ከነበረው አመለካከት የቀየረና 2.8 ሚሊዩን ዓመት ያስቆጠረ ቅሪተ አካል ተገኝቷል፡፡ ይህ በአፋር ክልል በታችኛው አዋሽ ሸለቆ ሌዲ ገራሮ በሚባል የመካነ መቃብር ስፍራ የተገኘው ቅሪተ አካል የሰው ዘር የታችኛው ከፊል የመንጋጋ ክፍል ሲሆን በስነ-ህይወት ምድብ ጂነስ ሆሞ (Genus Homo) መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ 



2ኛው ሀገር አቀፍ የግእዝ ጉባኤ

በሀገራችን ከሚገኙ ጥንታዊ ቋንቋዎች አንዱ ግእዝ ነው፡፡ በርካታ ታሪኮች በዚሁ ቋንቋ ሰፍረው ይገኛሉ፡፡ በግእዝ የተጻፉ መዛግብትን መርምሮ ለመጠቀም ቋንቋውን ማወቅና መጠቀም የግድ ቢልም የግእዝ ቋንቋ ተናጋሪዎችም ሆኑ አንባቢዎች በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ብቻ የሚገኙ እየሆኑ መጥተዋል፡፡ የዘመናዊ ትምህርት መስፋፋት ግእዝን ከብዙሃኑ ህዝብ አራራቀው፡፡ አሁን ባለንበት ዘመን ደግሞ ለግእዝ ባይተዋር የሆነ በሚሊዮን የሚቆጠር አዲስ ትውልድ ተፈጠረ፡፡ ቋንቋው ከቋንቋነት ባለፈ በያዛቸው ፋይዳ ያላቸው እውቀቶች፣ ሀገራዊ እሴት በመሆኑና ብቸኛው የአፍሪካ የራሱ ፊደል ያለው ቋንቋ በመሆኑ ሊጠበቅ ብቻ ሳይሆን ሊለማም ይገባዋል፡፡ ሁለተኛው የግእዝ ጉባኤም ይህንኑ ዓላማ መሰረት አድርጎ ከመጋቢት 22 እስከ 23 ቀን 2007 ዓ.ም በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል፡፡



ምዕራብ አርሲ ዞን
አብያታ ሻላ ብሔራዊ ፓርክ
የምዕራብ አርሲ ዞን ከአዲስ አበባ በ250 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኝ የስምጥ ሸለቆ አካባቢ ነው፡፡ 12409.99 ስኩየር ኪሎ ሜትር የቆዳ ስፋት ያለው ይህ ዞን በሰሜን ምስራቅ ሸዋ ዞን፣ በደቡብ ጉጂ ዞን፣ በምዕራብ የደቡብ ብሔረሰብ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል እና በምስራቅ ባሌ ዞን ያዋስኑታል፡፡ አብዛኞቹ የዞኑ አካባቢዎች አማካኝ ከባህር ጠለል (ወለል) በላይ ከ1500 እስከ 3800 ሜትር ከፍታ አላቸው፤ የዞኑ ዋና ከተማ ሻሸመኔ ነው፡፡ ከዞኑ ኢንቨስትመንት ቢሮ ባገኘነው መረጃ መሰረት የዞኑ የህዝብ ቁጠር ከ2 ሚሊየን በላይ እንዲሚሆን ይገመታል፡፡

Thursday, April 23, 2015

አራተኛው ዓለም አቀፍ የቱሪዝም የንግድ ትርኢት አውደ ርዕይ
ዛሬ ተከፈተ፡፡

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት አዘጋጅነት የሚሰናዳውና ዘንድሮ ከሚያዝያ 15 እስከ 19/2007 ዓ.ም የሚቆየው አራተኛው ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ንግድ ትርኢት በኤግዚቢሽን ማዕከል ዛሬ ከሰዓት በኋላ በድምቀት ተከፍቷል፡፡

የንግድ ትርኢቱን አዲሱ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅትና 50ኛ ዓመት ኢዩቤልዩውን እያከበረ ያለው የኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ስራ ድርጅትን ጨምሮ በርካታ አስጎብኚ ድርጅቶች፣ የአዲስ አበባ አስጎብኚ ማህበር፣ የተለያዩ ሆቴሎች፣ የእደ-ጥበብ አምራቾች፣ የክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮዎች ተሳትፈውበታል፡፡ አውደ ርዕዩ ለቀጣዮቹ አምስት ቀናት ለጎብኚዎች ክፍት ሆኖ ይቆያል፡፡

Thursday, April 16, 2015



የቦንጋ ብሔራዊ ቡና ሙዚየም ተመረቀ፡፡
በሀገራችን የመጀመሪያው የሆነውና በደቡብ ክልል ካፋ ዞን ቦንጋ ከተማ የሚገኘው ብሔራዊ የቡና ሙዚየም ሚያዝያ 6 ቀን 2007 ዓ.ም ተመርቋል፡፡ ይህ በጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ የተመረቀው ብቸኛው የቡና ሙዚየም በሚሌኒየሙ መሰረተ ድንጋዩ የተጣለ ሲሆን ዓላማውም ካፋ የቡና መገኛ መሆኗን ለማረጋገጥ፤ በሀገሪቱ ከቡና ጋር ተያይዞ የሚገኙ እሴቶችንና የቡናን ብዝሃ ህይወት የተመለከቱ ስብስቦችን ለማኖርና ለትውልድ ለማሻገር ሲሆን ከቡና ጋር ተያይዞ ምርምርና ጥናት ለሚያደርጉም ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ሙዚየም ነው፡፡ ደረጃውን የጠበቀው ብሔራዊ የቡና ሙዚየም ከዚህ በኋላ ለጎብኚዎች ክፍት ነው፡፡