Thursday, November 15, 2012


ዓለም አቀፍ የመቻቻል ቀን ዛሬ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቲያትር በሃገር አቀፍ ደረጃ ተከበረ!!!

በመድረኩ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበዋል፡፡

ዓለም በብዝሃነቷ የሚያውቃትን ያክል አብሮ የመኖርና የመተሳሰር እሴቶቿ ጎልተው ከወጡ ሃገራት መካከልም ትልቅ ስፍራ ይሰጣታል፡፡ ከመቻቻል ይልቅ  ከፍጹም ፍቅር በመነሳት አንዱ ለሌላው የሚኖርባት የወንድማማቾች ምድር የሆነችው ኢትዮጵያ እነሆ ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ ሃገር አቀፍ የመቻቻል ቀንን አክብራለች፡፡

ዛሬ በብሔራዊ ቲያትር በተዘጋጀው ሲምፖዚየም ላይ የተገኙት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ዳውድ መሐመድ አለመቻቻል አስከፊነቱና የሚፈጥረውን ስጋት ለመቀነስ የሁሉንም ዜጎች ቁርጠኝነት በየጊዜው ለማደስ ይህን ዝግጅት ማዘጋጀቱ አስፈላጊ እንደሆነ በእለቱ ዝግጅቱን ሲከፍቱ ባደረጉት ንግግር ገልጸዋል፡፡

አቶ አውላቸው ሹምነካ በሚኒስቴር መስሪያቤቱ የቋንቋና የባህል እሴቶች ልማት ዳይሮክተሬት ዳይሬክተር ዘንድሮ የሚከበረው በዓል የመቻቻል ባህላችንን በማጉላት ለዓለም ተምሳሌት  እንሆናለን በሚል መሪ ቃል  እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በእለቱ ዶ/ር ሀሰን ሰይድ፣ አቶ ተመስጌን ዩሐንስ፣  አቶ መርከብ መኩሪያ፣ አቶ ተሾመ ብረሃኑ ከማል ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡ ሲሆን ረዳት ፕሮፌሰር አህመድ ዘካሪያ ውይይቱን መርተውታል፡፡ በፕሮግራሙ ላይ የታደመው እንግዳ ከወትሮው በተለየ በርካታ እና ዝግጅቱም በብሄራዊ ቲያትር ባህል ቡድን የተዋዛ ነበር፡፡

Tuesday, October 9, 2012


በባህል ዘርፍ የሚሰሩ ባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ ሊመሰረት ነው፡፡

አመቻች ኮሚቴ ተዋቅሯል፤

በሃገራችን የባህል ዘርፍ ላይ የሚሰሩ ተቋማትን የሚያካትት የምክክር መድረክ ለማቋቋም ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በጠራው ጉባኤ ላይ ከዘርፍ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ስራ የሚሰሩ ተቋማትና ግለሰቦች ማክሰኞ መስከረም 29 ቀን 2005 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሆቴል በተደረገው የመጀመሪያ ጉባኤ ላይ ተካፍለዋል፡፡

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የስራ ኃላፊዎች በቀረቡ የመነሻ ጽሑፎች የባህል ፕላት ፎርም ምስረታ ዓላማዎች፣ በቋንቋና ባህል እሴቶች እና በባህል ኢንዱስትሪ ዘርፎች ሃገሪቱ በእድገት እና ትራንስፎርሜሽን ውጥኑ የአለመቻቸውን ግቦች የተመለከቱ መነሻ ጽሑፎች ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡

በተለያየ አግባብ ለማህበራዊ ትርፍና ለኢኮኖሚያዊ ትርፍ በመንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት በጥቅሉ ባህል ላይ ያተኮሩ ስራዎችን የሚሰሩ ባለድርሻ አካላትን በሙሉ ያካተተ የጋራ መድረክ ለመፍጠር እንዲቻል ስራውን የሚያከናውኑና የሚያመቻቹ አስራ አምስት አባላት በአመቻች ኮሚቴነት ተመርጠዋል፡፡

የተመረጠው ኮሚቴ አጠቃላይ የሆኑ የመመስረቻ ስራዎችን በማከናወን ብሔራዊ የባህል ባለድርሻ አካላት ምስረታ ጉባኤ አባላትን ለመጥራት አቅዷል፡፡

Wednesday, October 3, 2012


ማጫወት፣ መጋበዝ እና መውደድ የሚችለው የቤኒሻንጉል ጉምዝ ህዝብ

120 ሰዓታትን በደስታ

የ2005 ዓ.ም  የዓለም ቱሪዝም ቀን መስከረም 17 ቀን ተከብሯል፡፡ ሃገር አቀፍ ዝግጅት በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የተከበረ ሲሆን ከተከበረባቸው ስፍራዎች አንዱ ደግሞ የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ምድር ነው፡፡ ቱሪዝም ከዘላቂ የሃይል አቅርቦት ልማት ጋር ተቆራኝቶ እንዲከበር በመሪ ቃልነት የተከበረውን የዘንድሮ የቱሪዝም ቀን ለመታደም ቤኒሻንጉል ጉምዝ ከትመን ነበር፤

ከመተከል ዞን የጀመረው የሞቀ አቀባበል፣ እስከ ኦሮምያ ክልል ድንበር በዘለቀው የሽኝት ሥነ-ሥረዓት የ120 ሰዓታት እድሜ ነበረው፡፡ በዚህ እድሜ ውስጥ በዙምባራ ጥኡም ዜማ ታጅቦ የጉምዝ አያሌ ባህሎች ከልባችን ገብቷል፡፡ የበርታ እንግዳ አቀባበል፣ የኮሞ ጨዋታ የማኦ መስተንግዶ ስለቤኒሻንጉል ጉምዝ የምናወራውን እልፍ አድርጎታል፡፡

የቦሮ ሽናሻ ብሄረሰብ ከድንቅ ውዝዋዜው ጋር ቁርጡን እየመተረ መስቀሉን አብረንው እንድንታደም አድርጎናል፡፡ የማንኩሽ መስተንግዶ፣ የደጃዝማች ባንጃው ድንቅ እልፍኝ፣ የህዳሴው ምድር ውሎ አያሌ ትዝታዎች የታጨቁበት ጉዞ እንዲሆን አድርገውታል፡፡ ሀብታሙ ክልል አረንጓዴ ምድር እና ገና ያልተነገረ ታሪክ ያለው ነው፡፡

ተጫዋቹ፣ ተግባቢውና ለሰው ቅርብ የሆኑት የክልሉ ርእሰ መስተዳድር ከተገናኘንበት ቀን ጀምሮ እንግዳ ተቀባይ ህዝብ ብቻ ሳይሆን እንግዳ ተቀባይ አመራር እንዳለ አብነት ሆነው አሳይተውናል፡፡ ያዓ መሰራ እኩል ቀን ከገደልንባቸው መዳረሻዎች አንዱ ነበር፡፡ የሼህ ሆጀሌ ቤተ-መንግስት ጉብኝት የማንጎ ሎጅ መስተንግዶ እና መሰል የመዝናኛ ጊዜዎች አይረሴና መልካም ነበሩ ዓመቱን እንደ ወቅቱ እየቆነጠርን ለመተንተን እድሜና ጊዜ ይስጠን፡፡  

Saturday, September 22, 2012


የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ባህልና ቱሪዝም መምሪያዎችና ጽ/ቤቶች በባህር ዳር ከተማ ከትመው የዓመቱን አፈጻጸም ገመገሙ!

ጎንደር 1ኛ ደረጃነቷን  አስጠብቃለች፡፡

ምስራቅ ጎጃምና አዊ ዞን ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ ይዘዋል፡፡


ከመስከረም 7 ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ መስከረም 12 ቀን 2005 ዓ.ም ባህርዳር የተሰበሰቡት የባህልና ቱሪዝም ሴክተር ተቋማት በዋናነት ዓመታዊውን አፈጻጸማቸውን የገመገሙ ሲሆን መርሀ-ግብሩ በክልሉ ባህል፣ቱሪዝምና ፓርኮች ልማት ቢሮ የተዘጋጀ ነው፡፡

በአፈጻጸም ደረጃ ከአዲስ አበባና ከድሬዳዋ ቀጥሎ የቱሪዝም ዳይሮክተሪዋን ባስመረቀች ማግስት የጎንደር ከተማ አስተዳደር አንደኛ ደረጃን ይዛለች፡፡ በተያዘው ዓመት አያሌ የተለዮ ተግባራትን ያከናወነችው ጎንደር ከአዲስ አበባ ቀጥሎ የሙዚየም ቀን ተከብሮባታል፡፡ ከአማርኛ ቋንቋ ባሻገር በትግራይ በነበረው የከተሞች ቀን ላይ በትግርኛ ቋንቋ በተዘጋጁ የፕሮሞሽናል ቁሳቁሶች እራሷን ያስተዋወቀችው ጎንደር፤ በዚሁ ዓመት የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ባለድርሻዎችን ያካተተ የቱሪዝም ገቢ አመንጪ ኮሚቴ በማቋቋም ወደ ስራ የገባችበት ዓመት ነበር፡፡


Friday, September 14, 2012

tuba

መስቀል በአዲግራት

መስቀል በአዲግራት
 
መስቀል በሃገራችን በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት አንዱ ነው፡፡ በተለይም የደመራ በዓል ከፌስቲቫል ቱሪዝም ሀብታችን ውስጥ ግንባር ቀደሙን ቦታ ይይዛል፡፡ ይህንን በዓል የሰው ልጆች ሁሉ እሴት ለማድረግም ጥረቶች ተጀምረዋል፡፡ መስቀልን በዩኔስኮ ለመመዝገብ በቅቷል፡፡

መስቀል እንደ የኢትዮጵያውያን እሴትና ባህል ከዳር ዳር የሚከበር ከአደይ ጋር አብሮ የሚፈካ፣ ከዘመን ጋር የሚጠባ በዓል በመሆኑ ይበልጥ ደማቅ እንዲሆን አድርገዋለል፡፡

በድንቅ እሴት የተሞላውና ብዙ ሳይነገርለት የኖረው የምስራቃዊ ትግራይ ዞን የመስቀል በዓል አንዴ ሌላ የባህል ሃብት መስህባችን ነው፡፡