Monday, December 8, 2014


ነቀምቴ ከተማ

ነቀምቴ ከተማ የምስራቅ ወለጋ ዞን ርዕሰ ከተማ ስትሆን በስድስት ክፍለ ከተሞች የተከፋፈለች ናት፡፡ በከንቲባ ደረጃ በ1830 ዓ.ም አካባቢ በዘመኑ ገዥ በነበሩ በደጅ አዝማች ሞሮዳ በከሬ ጎዳና የተመሰረተችው ነቀምቴ ነቀምቴ የሚለውን ስያሜዋን ያገኘችው ቀደም ሲል በቦታው ላይ ይኖሩ ከነበሩ (ነቀምቴ ገዳአታ- መጫ) በሚባሉ ሰው ስም እንደሆነ ይነገራል፡፡ በወቅቱ በከፍተኛ ግምት የሚሰጠው የሲራራ ንግድ ከምፅዋ እስከ ማጂ-ከፋ ወርቅ፣ የባሪያ፣ የዝሆን ጥርስ፣ የጥርኝ የነብር ቆዳና የጨሌ ነጋዴዎች መመላለሻና መለዋወጫ ከዚያም የከብት የእህልና የተለያዩ ሸቀጦች መተላለፊያ ማእከል እንደነበረች ታሪክ ያወሳል፡፡ በ1937 ዓ.ም. በ18 ጋሻ መሬት ላይ የተቆረቆረችው ነቀምቴ በማዘጋጃ ቤት ደረጃ በከተማነት ተመዝግባ ህጋዊ እውቅና ያገኘችው ግን በ1942 ዓ.ም. ነው፡፡
ሶርጋ ሰው ሰራሽ ሀይቅ
 

ያሶ ወረዳ

በካማሺ ዞን ከሚገኙ አምስት ወረዳዎች መካከል አንዱ ሲሆን በ13 ቀበሌያት የተዋቀረ ነው፡፡ የወረዳው ቆዳ ስፋት 2858 ስኩዬር ካሬ ሜትር ሆኖ ከባህር ወለል በላይ ከ1200-2000 ሜትር ከፍታ አለው፡፡ መልካ ምድራዊ አቀማመጡም 50 በመቶ ሜዳማ፣ 30 በመቶ ተራራማ እና 20 በመቶ ሸለቆአማ ሲሆን የአየር ንብረቱ 91.8% ቆላማ እና 8.2%  ደግሞ ወይና ደጋ ነው፡፡ አማካይ የወረዳው የዝናብ መጠን ከ1200-1800 ሚሊ ሜትር ይጠጋል፡፡  የሙቀት መጠኑ በአማካይ 35ċ እንደሚሆንም ይገመታል፡፡ በ2005 ቆጠራ የወረዳው ህዝብ ብዛት ወንዶች 16082 ሴቶች 3581 ሲሆን በድምሩ 19663 ይሆናል፡፡ 
 

በወረዳው ታሪካዊና ተፈጥሮአዊ የመስህብ ሀብቶች ባለቤት ሲሆን ከነዚህም አያሙሳ ውሀ፣ ባጨጋንት ተራራ፣ ኮሚጳፍል ውሀ፣ የተፈጥሮ ዋሻ፣ ግሽሚላ ድንጋይ፣ ዳዱ ፏፏቴ፣ ፈወለወ ውሀና ቦንቅሽ ፓርክ ይገኙበታል፡፡

ማኦ ኮሞ

የማኦ ኮሞ ልዩ ወረዳ በቤኒሻምጉል ጉምዝ ክልላዊ መንግስት ደቡብ ምዕራባዊ ክፍል የሚገኝ ሲሆን ከአሶሳ በ115 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ የወረዳው ዋና ከተማ ቶንጎ ሲሆን የወረዳው አጠቃላይ የቆዳ ስፋት 210,000 ሄክታር እንደሚሆን ይገመታል፡፡ ልዩ ወረዳው በምዕራብ ከሱዳን፣ በሰሜን ከአሶሳ፣ በደቡብ ከጋምቤላ ክልል በምስራቅ ደግሞ ከኦሮምያ ክልል ጋር ይዋሰናል፡፡ በልዩ ወረዳው በዋናነት የማኦ፣ ኮሞ፣ በርታና ሌሎች ብሔረሰቦች የሚኖሩበት ሲሆን በ32 ቀበሌ የተዋቀረ ነው፡፡ የወረዳው ህዝብ ብዛት ከ63,000 በላይ እንደሚሆን የተለያዩ የሰነድ ማስረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በወረዳው የተለያዩ ባህላዊ ተፈጥሮአዊና ታሪካዊ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎች ይገኛሉ፡፡ ጥቂቶቹን በዚህ ዘገባ በጥቂቱ እንቃኛቸዋለን፡፡

ሸሞሎ ተራራ
 

መተከል ዞን

የመተከል ዞን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት ውስጥ ከሚገኙት ሶስት ዞኖች አንዱ ሲሆን በሰሜንና በምስራቅ ከአማራ ክልል፣ በደቡብ፣ በካማሽ /አባይ ወንዝ/ በምዕራብ ከሱዳን ጋር ይዋሰናል፡፡ በዞኑ በዋናነት የጉሙዝና የሽናሻ ብሄረሰቦች የሚኖሩ ሲሆን የኦሮሞ፣ የአማራ፣ የአገውና ሌሎች ብሄረሰቦች ማህበራዊ ትስስር በመፈጠር አብሯቸው ይኖራሉ፡፡ የዞኑ ዋና ከተማ ግልገል በለስ በቅርብ ጊዜ በ1993 ዓ.ም. የተቆረቆረች ከተማ ብትሆንም አካባቢዋ ለልማት ምቹ ከመሆኑ አኳያ የተፈጠረው ዕድገትና ለውጥ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡
 

የካማሺ ዞን

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከሚገኙት 3 ዞኖች መካከል አንዱ ነው፡፡ የዞኑ ዋና ከተማም ካማሽ ትባላለች፡፡ የክልሉ ርዕሰ ከተማ ከሆነችው አሶሳ በስተደቡብ ምስራቅ አቅጣጫ በ246 ኪሎ ሜትር ከአዲስ አበባ በስተምዕራብ አቅጣጫ ደግሞ በ512 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡
ጀሎ ተራራ ካማሽ ወረዳ ጀሎ ሌቃ ቀበሌ
 

የዞኑ ህዝብ ቁጥር 128,632 ሲሆን በአምስት ወረዳዎችና በ65 ቀበሌዎች የተደራጀ ነው፡፡ ዞኑን በደቡብ እና በምስራቅ ኦሮሚያ ክልል በሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ ከአሶሳና ከደቡብ ሱዳን እንዲሁም በሰሜን ከመተከል ዞንና ከአማራ ክልሎች ጋር ይዋሰናል፡፡ የአየር ንብረቱ ቆላማ ሲሆን በዞኑ በብዛት ሰፍሮ የሚገኘው የጉሙዝ ብሄረሰብ ነው፡፡

Wednesday, September 17, 2014


የቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኃኒዓለም ሙዚየም
የልጅ እያሱ አልጋ
 

አዲስ አበባ ከሚገኙ 14 ሙዚየሞች አንዱ የቀጨኔ ሙዚየም ነው፡፡ ቀጨኔ ሙዚየም በአስተዳደር ጊዜያቸው ለህብረተሰቡ ኑሮ ምቹ ከመሆናቸው የተነሳ አቤቶ (ማር) የሚል ስያሜ የተሰጣቸው ልጅ እያሱ ከመቶ ዓመት በፊት  ቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን ካሳነፁ በኋላ የተቋቋመ ሙዚየም ነው፡፡ በሙዚየሙ ውስጥ ከሚገኙ ቅርሶች ብዙዎቹ የልጅ እያሱ የግል መገልገያ እቃዎች፣ ነዋየ ቅድሳት፣ አልባሳት እና የተለያዩ ነገስታት ስጦታዎች ይገኛሉ፡፡

በናና ጸማይ…..


 
በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ደቡብ ኦሞ ዞን ስር ከተዋቀሩት 8 ወረዳዎችና አንድ የከተማ አስተዳደር መካከል የበናና ፀማይ ወረዳ አንዱነው፡፡ የወረዳው ዋና ከተማ ቀይ አፈር ከዞኑ ዋና ከተማ ጂንካ በስተደቡብ ምስራቅ አቅጣጫ በ42 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ወረዳው በሰሜን ከደቡብ አሪ እና ማሌ፣ በደቡብ ከሐመር ወረዳ፣ በስተምስራቅ ከኮንሶ በምዕራብ ከማጎ ፓርክ እና ሳላማጎ ወረዳ ጋር ይዋሰናል፡፡ በዞኑ ከሚገኙት 16 ብሔረሰቦች ውስጥ በዋናነት ሶስቱ ብሔረሰቦች የሚገኙት በዚህ ወረዳ ውስጥ ነው፡፡ እነዚህም የበና፣ የፀማይ እና የብራይሌ ብሔረሰቦች ናቸው፡፡

አፋር ያልተነገረላቸው ሁሉ አቀፍ የቱሪስት መስህቦች ቀጠና

የአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በኢትዮጵያ ከሚገኙ 9 ክልሎችና 2 ከተማ መስተዳደሮች አንዱ ነው፡፡ ክልሉ ጂኦግራፊካሊ በሰሜን ምስራቅ ኢትዮጵያ በ39 14 እና 42 28 ሰሜን የኬክሮስ መስመርና በ8 49 እና በ14 30 ምስራቅ የኬንትሮስ መስመሮች ይገኛል፡፡
Afar-
 

የአፋር ክልል በ5 አስተዳደራዊ ዞኖች 31 ወረዳዎችና በ1 ልዩ ወረዳ የተዋቀረ ነው፡፡ የቆዳ ስፋቱም 96,256 ስኩየር ኪ.ሜ ነው፡፡  እንደ ኢትዮጵያ ማእከላዊ ስታስቲክስ 2007 መረጃ መሰረት 1,411,920 ህዝብ ይኖርበታል፡፡ ከዚህም 86.6% በገጠር ቀሪው በከተማ የሚኖር ህዝብ ነው፡፡ አፋርኛ ቋንቋ የክልሉ የስራ ቋንቋ ሲሆን 90.8% ተናጋሪዎች አሉት፡፡

Tuesday, August 26, 2014


         አሸንዳ - የሰሜናዊቷ ኮከብ ከተማ ኮከብ ኩነት

 

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኞች ዘንድ የጾመ ፍልሰታ ፍጻሜን ተከትሎ የሚከበረው የአሸንድዬ በዓል በዋናነት በሰሜን ኢትዮጵያ ከሚከበሩ መንፈሳዊ በዓላት መካከል የሚጠቀስ ነው፡፡ የአሸንዳ ባህላዊ ጨዋታ መጠሪያ የኾነው ቄጤማ ረዥምና ለምለም እንደ ቅጠል ሰፋ ያለ ሲሆን ቁመቱ 80 እስከ 90 . ይኾናል፡፡

የአሸንዳ በዓል በትግራይ ብሔራዊ ክልል የሚከበር በሀገራችን ከሚገኙ ኩነቶች አንዱ ነው፡፡ አሸንዳ ጥንታዊና የልጃገረዶች ባህላዊ በዓል ነው፡፡ በተለይም ከአዲስ አበባ በ783 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው የክልሉ መዲና መቐለ በየዓመቱ የምታስተናግደው ይህ ፌስቲቫል ከትግራይ ወጣቶች ባለፈ ጎብኚዎችም በጉጉት የሚጠብቁት ባህላዊ ትዕይንት ሆኗል፡፡

Thursday, August 21, 2014


የአሸንዳ በዓል ዓመታዊ ኩነት በሰሜናዊቷ መቐለ መከበር ጀምሯል፡፡

ቱባ-መቐለ
 

በየዓመቱ የአሸንዳ በዓል በድምቀት የሚከበርባት የትግራይ ክልል መዲና ዘንድሮም በተመሳሳይ መልኩ በዓሉን ለማክበር ሰፊ ዝግጅት ስታደርግ ቆይታለች፡፡ ዛሬ ነሐሴ 15 ቀን 2006 ዓ.ም የአሸንዳ በዓል ዓመታዊ ኩነት ጀምሯል፡፡ ጠዋት በሚላኖ ሆቴል ለግማሽ ቀን በአሸንዳ ላይ የመከረው ሲምፖዚየምም የዚሁ ዝግጅት አካልና በትግራይ ባህልና ቱሪዝም ኤጀንሲ የተዘጋጀ ነው፡፡ ከሰዓት ደግሞ የመቐለ ጎዳናዎች በአሸንዳ ጨፋሪዎች ይደምቃሉ፡፡ ነገ የሚከናወነው ዋናው የአሸንዳ በዓል ዝግጅት ነው፡፡
 

Friday, August 8, 2014


የፎቶና ቪዲዮ ባለሙያዊ አዚዝ አህመድ ድንቅ ሥራዎች ተመረቁ፡፡
 

ፕሮፌሽናል የጉዞ ፎቶ ግራፈሩና የቪዲዮ ባለሙያ የሆነው አዚዝ አህመድ በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር ያነሳቸው የአእዋፍ ፎቶ ምስሎችና የሀገራችንን የተፈጥሮ ሀብቶች የሚያሳየውን የአጭር ድምጽና ምስል የቱሪዝም ዘጋቢ ፊልሙን ትናንት ነሐሴ 1 ቀን 2006 ዓ.ም ከቀኑ 9፡30 ላይ በአዲስ አበባ ካፒታል ሆቴል አስመርቋል፡፡

ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመተባበር የተዘጋጀው ይህ በኢትዮጵያዊ በዚህ መልኩ ሲሰራ የመጀመሪያ ሊባል የሚችለው ድንቅ ስራ ክቡር አቶ አሚን አብዱልቃድር የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር፣ ክቡር አቶ እውነቱ ብላታ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር ዴኤታ እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ የሆኑት ዶ/ር ይናገር ደሴ በተገኙበት ተመርቋል፡፡

የጉዞ ፎቶግራፈሩ ጥንካሬ እውን ያደረጋቸው እነኚህ የኢትዮጵያን እምቅ የተፈጥሮ መስህቦች የሚያስተዋውቁ ስራዎች በሀገራችን ቱሪዝም ልማት ጎብኚዎችን በመሳብ የሚኖራቸው ፋይዳ ከፍተኛ ነው፡፡ ዶክመንተሪውም በኢትዮጵያ አየር መንገድ ለአየር መንገደኞች በመቅረብ ላይ ያለ መሆኑን ስራውን ከደገፉት አንዱ የሆኑት የፍራንክፈርት ዙኦሎጂካል ሶሳይቲ ሃላፊ ዶ/ር ዘላለም ገልጸዋል፡፡

አዚዝ አህመድ በተለየ መልኩ ትኩረታቸውን በአእዋፍና ተፈጥሮ መስህቦች ዙሪያ አድርጎ በመስራት ስኬታማ ከሆኑ ኢትዮጵያዊ የፎቶግራፍ ባለሙያዎች አንዱ ነው፡፡  

Wednesday, July 23, 2014


የሲዳማ ዘመን መለወጫ በዓል በሐዋሳ እየተከበረ ነው፡፡

የራሳቸው የቀን አቆጣጠር ካላቸው የሀገራችን ብሔሮች አንዱ የሆነውና በየዓመቱ በልዩ ድምቀት የዘመን መለወጫ በዓሉን የሚያከብረው የሲዳማ ብሔረሰብ የፍቼ በዓል በታላቅ ድምቀት በሐዋሳ እየተከበረ ነው፡፡


ዝግጅቱ በዋናነት ዛሬ ሐምሌ 16 ቀን ከሰዓት በኋላ በሲዳማ ባህል አዳራሽ በታላቅ ድምቀት መከበሩን የቀጠለ ሲሆን በዝግጅቱም ላይ የትምህርት ሚኒስትሩ አቶ ሽፈራሁ ሽጉጤ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደሴ ዳልኬ እና የሲዳማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ የብሔረሰቡ ምሁራንና ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶች ታድመውበታል፡፡
ዝግጅቱን በተመለከተ የሲዳማ ዞን ባህል ቱሪዝምና መንግስት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ሃላፊ አቶ ወርቅነህ ፍላቴ ሲናገሩ፤ ፍቼ በቅርብ ጊዜ ኢትዮጵያ በዩኔስኮ የምታስመዘግበው ዓለም አቀፍ ቅርስ ይሆናል ብለዋል፡፡
 
በዓሉ በነገው ዕለትም ቀጥሎ የሚውል ሲሆን የበዓሉ ዋና መዲና ሐዋሳ በዓሉን በከፍተኛ ዝግጅት እያስተናገደችው ነው፡፡