Monday, December 8, 2014


ነቀምቴ ከተማ

ነቀምቴ ከተማ የምስራቅ ወለጋ ዞን ርዕሰ ከተማ ስትሆን በስድስት ክፍለ ከተሞች የተከፋፈለች ናት፡፡ በከንቲባ ደረጃ በ1830 ዓ.ም አካባቢ በዘመኑ ገዥ በነበሩ በደጅ አዝማች ሞሮዳ በከሬ ጎዳና የተመሰረተችው ነቀምቴ ነቀምቴ የሚለውን ስያሜዋን ያገኘችው ቀደም ሲል በቦታው ላይ ይኖሩ ከነበሩ (ነቀምቴ ገዳአታ- መጫ) በሚባሉ ሰው ስም እንደሆነ ይነገራል፡፡ በወቅቱ በከፍተኛ ግምት የሚሰጠው የሲራራ ንግድ ከምፅዋ እስከ ማጂ-ከፋ ወርቅ፣ የባሪያ፣ የዝሆን ጥርስ፣ የጥርኝ የነብር ቆዳና የጨሌ ነጋዴዎች መመላለሻና መለዋወጫ ከዚያም የከብት የእህልና የተለያዩ ሸቀጦች መተላለፊያ ማእከል እንደነበረች ታሪክ ያወሳል፡፡ በ1937 ዓ.ም. በ18 ጋሻ መሬት ላይ የተቆረቆረችው ነቀምቴ በማዘጋጃ ቤት ደረጃ በከተማነት ተመዝግባ ህጋዊ እውቅና ያገኘችው ግን በ1942 ዓ.ም. ነው፡፡
ሶርጋ ሰው ሰራሽ ሀይቅ
 

በከተማዋ ውስጥ የመሰረተ ልማት አውታሮች እየተስፋፉ በመሄዳቸው ከተለያዩ ማዕዘናት ያሉ ህዝቦች የተሻለ ማህበራዊ አገልግሎት ለማግኘት በሚደረገው ፍሰት የህዝቧ ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ በ1968 ዓ.ም. የእድገት ፕላን የተሰራላት ሲሆን ስፋቷም 3192 ሄክታር ነበር፤ በዘመናዊ ሁኔታ እድገቷን ለማፋጠን እንደገና በ2001 ዓ.ም. ዳግም የእድገት ፕላን የተሰራላት ሆኖ በአሁኑ ግዜ ስፋቷ 5380 ሄክታር ይደርሳል፡፡
ነቀምቴ ከአዲስ አበባ በ328 ኪ.ሜ. ርቀት በስተምዕራብ አቅጣጫ ትገኛለች፡፡ በደቡብ ምዕራብ ኦሮምያ ለሚገኙ የሀገሪቱ ክልሎች አዋሳኝ ቦታ ላይ ናት፡፡ ካላት 5380 ሄክታር ውስጥ 27 በመቶ ሜዳማ 66.6 በመቶ ወጣ ገባ 0.33 በመቶ ረግረጋማ እና 5.76 በወንዞች የተሸፈነ መሆኑን በከተማ ማስተር ፕላን ላይ መረዳት ይቻላል፡፡
ነቀምቴ በምዕራብ ኦሮምያ ከሚገኙ ከተሞች ትልቋ ከተማ ናት፡፡ አቀማመጧም በአራቱም አቅጣጫ የሚያቋርጧት መንገዶች አሉ፡፡ እነሱም ከአዲስ አበባ ነቀምቴ፣ ከጅማ ነቀምቴ፣ ከአሶሳ ነቀምቴ እና ከባህርዳር ነቀምቴ ናቸው፡፡
የህዝብ ብዛት የኦሮምያና የፌደራል ስታትስቲክስ በገለፀው መሰረት የነቀምቴ ከተማ ህዝብ ብዛት 76817 ሲሆን አሁን ባለው የመንግስትና የግል ተቋማት መስፋፋት ጋር ተያይዞ የህዝቧ ቁጥር በመጨመሩ በአሁን ሰዓት እስከ 100,000 ይደርሳል ተብሎ ይገመታል፡፡ የከተማው የስራና የትምህርት ቋንቋ አፋን ኦሮሞ ሲሆን አማርኛ፣ ትግርኛ እና ጉራጊኛ በብዛት ይነገሩባታል፡፡

የቱሪዝም መስህቦች በነቀምቴ
ወለጋ ሙዚየም፣ ታዋቂው የደጃዝማች ኩምሳ ሞሮዳ ቤተመንግስት እና በግቢው ውስጥ ለተለያዩ አገልግሎት የተሰሩት ጥንታዊና ታሪካዊ ቤቶች፣ ሶርጋ ሰው ሰራሽ ሀይቅ መዝናኛ ስፍራ፣ ወለጋ ስታድየም፣ የተለያዩ የእምነት ስፍራዎች  ተጠቃሾች ናቸው፡፡
ወለጋ ሙዚየም፡- ሙዚየሙ በ1975 ዓ.ም. መሰረተ ድንጋይ ተጥሎ በ1979 ዓ.ም. ተሰርቶ ተከፍቷል፡፡ የተሰራው ከህዝብ በተዋጣ በ380,000 ብር ሲሆን በውስጡ ሶስት የቅርስ ማሳያ አዳራሾች፣ ፎቶ ላይብረሪ ክፍል፣ የአስተዳደርና የአስጎብኚ ክፍሎች አሉት፡፡ በግቢው ውስጥ የኢጣሊያ ጦር፣ አውሮፕላን ሞተር ባህላዊ ቤቶች፣ የተለያዩ ዛፎች ይገኛሉ፡፡
ሶርጋ ሰው ሰራሽ ሀይቅ፡- ይህ ሰው ሰራሽ ሀይቅ ከከተማው በ3 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ሲገኝ በ1980ዎቹ ውስጥ በሉተራን ሚሽነሪ የተሰራ ሲሆን ስያሜውን ያገኘው ከአካባቢው ነው፡፡ አጠቃላይ ያረፈበት ካሬ ስፋት 62 ሄክታር ሲሆን ጥልቀቱ 20 ሜትር ነው፡፡ ዙሪያውን በደን ተሸፍኖ የጀልባ አገልግሎትም ያለው ነው፡፡ ሰው ሰራሽ ሀይቁ ከተፈጥሮ ጋር ተዳምሮ አረንጓዴነቱና የአእዋፋቱ ዝማሬ ልብን ያማልላል፡፡

የታዋቂው የደጃዝማች ኩምሳ ሞሮዳ ቤተ መንግስት
ይህ ቤተ መንግስት የተመሰረተው በ1830 ሲሆን ከቤተመንግሰቱ በተጨማሪ በግቢው ውስጥ ለተለያዩ አገልግሎት የሚውሉ ቤቶች አሉ፡፡

ችሎት ቤት
ይህ  ቤት  ለዳኝነት ወይም ለፍትህ ጉዳዮች አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ ሲሆን የፍትህ አካላት በተሰጡ ውሳኔዎች ላይ የሚቀርቡ ይግባኞችም የሚታዩበት ቤት ነው፡፡

የፈረንጅ ማዕድ ቤት
የፈረንጅ ማዕድ ቤት ተብሎ የሚጠራው ወደ ቤተ መንግስታቸው የሚመጡ የውጭ ዜጎች (ፈረንጆች) የአካባቢው ምግብ አልስማማ ብሏቸው እንዳይቸገሩ ታስቦ የተሰራ ሲሆን የፍላጎታቸውን ለመጠበቅ ሲባል እነሱ የሚፈልጉት ታርዶም ሆነ ሌላ የቀረበላቸውን ራሳቸው የሚያበስሉበት ቤት ነበር፡፡

የገንዘብ ቤት
በንጉሱ ቤትና በሴቶች መኖሪያ መካከል ድብቅ በሆነ ቦታ ላይ የተሰራ ነው፡፡ ይህ ክፍል በዓይነት የሚከፈለውን ግብር እንደ ማርትሬዛ፣ ጠገራ፣ ብር፣ ወርቅ፣ የዝሆን ጥርስ፣ ዝባድ የመሳሰሉት የሚጠበቁበት ዘመናዊ ባንክ መሰል ነው፡፡ ክፍሉ ወደ ታች የሚገባና ከምድር በታች በሁለት ደረጃ ቤት የተከፈለ ሲሆን ለመኖርም ሆነ ለማስወጣት በመሰላል ይገለገሉ ነበር፡፡

ማዕድ ቤት
ይህ ቤት የተለያዩ የአካባቢው ህብረተሰብ ባህላዊ ምግቦች በቤተመንግስቱ ውስጥ ለሚኖሩም ሆነ ለእንግዶች የሚዘጋጅበት የማዕድ ቤት ነው፡፡

የወንድ እልፍኝ
ይህ የወንድ እልፍኝ የሚባለው የኦሮሚያን የገዳ ስርዓት ጠብቆ ባለ 8 በር ሆኖ የተሰራ ሲሆን ለንጉሱም ሆነ ለንጉሱ ቅርበት ያላቸው ሰዎች የግል ጉዳዮቻቸውን ለማቅረብ፣ እንዲሁም ከታዋቂ ሰዎች ጋር ለመመካከር የሚገለገሉበትና የሚስተናገዱበት ቤት ነው፡፡

የሴት እልፍኝ
ይህ የሴት እልፍኝ የወለጋ ኦሮሞን  ባህላዊ የቤት አሰራር ጠብቆ ባማረ ሁኔታ በተመረጡ የቤት መስሪያ ቁሶች የተሰራ ነው፡፡ ጣሪያውና ገበታው በአካባቢው ከሚገኙውበትና ጥንካሬ ባላቸው እቃዎች ተመርጦ የተሰራ ሲሆን አገልግሎቱም በዋናነት ለንጉሱ ሚስት መኖሪያና እንግድነትም ሆነ ጉዳይ ኖሯቸው የሚመጡ ሴቶች የሚስተናገዱበት ነው፡፡

የስጦታ ቤት
ይህ የስጦታ ቤት ለንጉሱ ክብር ሲባል በስጦታ የሚመጡ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች፣ አልባሳት፣ የወግ እቃዎች እና ሌሎች ተዛማጅ ስጦታዎች የሚከማቹበትና የሚጠበቁበት ቤት ነበር፡፡

የግብር አዳራሽ
ሰፊ አዳራሽ ሲሆን የተሰራውም በኩምሳ ልጅ በደጃዝማች ሀብተ ማርያም ኩምሳ ነበር፡፡ አዳራሹ ለገዢው ቅርበት ከነበራቸው ታላላቅና ታዋቂ ሰዎች፣ የጦር መኮንኖችና አንባቢው ህብረተሰብ ከእነዚህ ክፍሎች ለግብዣው የሚቀርቡ ጠጅ፣ ሥጋ፣ እንጀራ እና የመሳሰሉት የሚቆዩበት ሰፋፊ ክፍሎች አሉ፡፡

የማርያም ቤተ ክርስትያን
ቤተክርስቲያኑ የተመሰረተው በ1883 ሲሆን ያሰሩት ኩምሳ ሞሮዳ ናቸው፡፡ በፊት ቤተክርስቲያኑ ሲሰራ የሳር ቤት ሲሆን አሁን ያለው ህንጻ ቤተክርስትያን የተሰራው በ1924 ዓ.ም. ነው፡፡ ይህ ታሪካዊ ቤተ ክርስቲያን በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ድጋፍና በምእመናኑ መዋጮ በ1999  ጥገና የተደረገለት ሲሆን ጥገናውም ታህሳስ ተጀምሮ ሀምሌ በር ላይ ተጠናቋል፡፡ በቤተክርስቲያኑ ውስጥ የተለያዩ ንዋየተ ቅድሳት ቢኖሩም ሙዚየም ባለመሰራቱና በስርዓት ባለመቀመጡ ለብልሽት እየተዳረገ ይገኛል፡፡ ከነዚህ ቅርሶች ውስጥ ረዥም ዓመት ያስቆጠሩ የተለያዩ የብራና መፅሀፍት፣ የነገስታቱ አልባሳት እና መገልገያ እቃዎች፣ ዘውድ፣ መቋሚያ፣ አርዌ ብረት፣….. ይገኙበታል፡፡ ሌላው በቤተክርስቲያኑ ቅጥር ጊቢ  ውስጥ የሚገኘው የነገስታቱ መካ መቃብር ነው፡፡

የአነሲሞስና የአስቴር መካነ መቃብር ስፍራዎች
የመጀመሪያውን የአፋን ኦሮሞ መፅሐፍ ቅዱስ የተረጎሙት አነሲሞስ አዲስ ኪዳንን በ1885 ዓ.ም. ብሉይ ኪዳንን በ1888 ዓ.ም. ወደ አፋን ኦሮሞ ተርጉመው እንደጨረሱ የስብከት አገልግሎት ሲሰጡ ቆይተው በ1942 ዓ.ም. የህዳር ወር መጀመሪያ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩትና የረዳታቸው አስቴር መካ መቃብር በነቀምቴ ከተማ የነቀምቴ መካነ እየሱስ ማህበረ ምዕመናን ቤተክርስቲያን ይገኛል፡፡

በከተማው ውስጥ የሚገኙ የኦሮሞ ባህላዊ ምግቦችና መጠጦች
አንጮቴ፡- እንሶስላ መሳይ የስር ተክል ሲሆን አሰራሩም ይታጠብና ይፋቃል፤ ከዛም ይቀቀልና ይለነቀጣል (ይፈጫል) የተፈጨውን አንጮቴ በቅመም በተነጠረ ንፁህ ቅቤ ይለወስና ከአይብ /ከእርጎ/ ጋር በማቅረብ ይበላል፡፡ ለመስቀል በዓል የሚዘጋጀው ግን የተቀቀለውን አንጮቴ በመሰነጣጠቅ በቆጭቆጫ ይበላል፡፡
ቡነ-ቀላ፡- ገብስ ተፈትጎ ከተቆላና ተሸክሽኮ ከገለባው ከተለየ በኋላ ትንሽ ሚጥሚጣ በማድረግ በጥሬ ቅቤ ድፍን ቡና ከነገለባው በቂቤ ተጠብሶ ከቆሎው ጋር በመቀላቀል ይበላል፡፡
ጨጨብሳ፡- የጤፍ ቂጣ ተጋግሮ ተሰባብሮ በቅመም በተነጠረ ንፁህ ቅቤ ይለወስና ይበላል፡፡
ቆሪ፡- ገብስ ተፈትጎ፣ ተቆልቶ፣ ተሸክሽኮ ከገለባው ከተለየ በኋላ በተነጠረ ቅቤ ይታሽና በማንኪያ ይበላል፡፡
ጭኮ፡- ከገብስ የተዘጋጀ የበሶ ዱቄት በቅቤ በመለወስ እየተቆረሰ የሚበላ የምግብ ዓይነት ነው፡፡
ቆጭቆጫ፡- ቃርየ፣ ዝንጅብል፣ ነጭ ሽንኩርት፣ ኮረሪማ፣ በሶቢላ አንድ ላይ በመለንቀጥ የሚዘጋጅ የምግብ ማባያ ነው፡፡
ቡቁሪ፡- ከዳጉሳ፣ ከጤፍ ወይም ከበቆሎ ዱቄት ተቦክቶ ይጎበጎብና ይጋገራል፤ ብቅል ተመጥኖ ይገባበትና አሪፍ ባህላዊ መጠጥ ይሆናል፡፡ የቡልቡላዳ (ብርዝ) መጠጥ ወዘተ ተጠቃሾች ናቸው፡፡

የኢንቨስትመንት አማራጮች

ከተማዋ በአራት በር የትራንስፖርት አገልግሎት ያላት በመሆኗ ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ ይታይባታል፡፡ አካባቢው በወርቅና በቡና ምርት ከመታወቁና የቱሪዝም ቀጠና መሆን የምትችል ከተማ ናት፡፡ ከዚህ ጋር ተዳምሮ  ከፍተኛ የሰው ፍሰት ያለባት ቀጠና በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ግንባታ ለሚሰማራ ምቹ አማራጭ ይሆናል፡፡

No comments:

Post a Comment