ማኦ ኮሞ
የማኦ ኮሞ ልዩ ወረዳ በቤኒሻምጉል ጉምዝ ክልላዊ መንግስት ደቡብ ምዕራባዊ ክፍል የሚገኝ ሲሆን ከአሶሳ በ115 ኪ.ሜ
ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ የወረዳው ዋና ከተማ ቶንጎ ሲሆን የወረዳው አጠቃላይ የቆዳ ስፋት 210,000 ሄክታር እንደሚሆን ይገመታል፡፡
ልዩ ወረዳው በምዕራብ ከሱዳን፣ በሰሜን ከአሶሳ፣ በደቡብ ከጋምቤላ ክልል በምስራቅ ደግሞ ከኦሮምያ ክልል ጋር ይዋሰናል፡፡ በልዩ
ወረዳው በዋናነት የማኦ፣ ኮሞ፣ በርታና ሌሎች ብሔረሰቦች የሚኖሩበት ሲሆን በ32 ቀበሌ የተዋቀረ ነው፡፡ የወረዳው ህዝብ ብዛት
ከ63,000 በላይ እንደሚሆን የተለያዩ የሰነድ ማስረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በወረዳው የተለያዩ ባህላዊ ተፈጥሮአዊና ታሪካዊ የቱሪዝም
መዳረሻ ስፍራዎች ይገኛሉ፡፡ ጥቂቶቹን በዚህ ዘገባ በጥቂቱ እንቃኛቸዋለን፡፡
ሸሞሎ ተራራ |
1ኛ. ያአ መስሪያ ታሪካዊ መስጊድ፡-
የአበል ድግስ ቀበሌ ውስጥ የሚገኘው ይህ ታሪካዊ መስጊድ የተቋቋመው በ1942 ከናይጄርያ በመጡ በአልፊኪ አህመድ ኡመር
በተባሉ ታላቅ የእስልምና ሀይማኖት መሪ አማካኝነት ነው፡፡ እኚህ ሰው ከናይጄሪያ ጅማ፣ ከጅማ ደንቢዶሎ በመጓዝ በመጨረሻም በራእይ
ታይቷቸው በታያቸው አቅጣጫ መጥተው መስጊዱን እንዳቋቋሙት ይነገራል፡፡ በዓመት ከ30,000 እስከ 31፻000 የሀገር ውስጥና ከሀገር
ውጪ የሚመጡ ቱሪስቶች እና የሀይማኖት ተከታዮች ይጎበኙታል፡፡ በተጨማሪም ለወረዳው ለመጀመሪያ ግዜ የመብራት እና የወፍጮ አገልግሎት
እንዲያገኝ ያደረጉት እኚህ ታላቅ ሰው ሲሆኑ መብራቱም በውሀ ሀይል የሚሰራ ነው፡፡
2ኛ. ሆሮ ጉባ ፍል ውሀ ፡-
በላቂ ቀበሌ ሲገኝ በግምት ከቶንጎ በ30 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ፍል ውሀ ለተለያየ ደዌ መፈወሻነት ሲጠቀሙበት
ከዚህ በተጨማሪም ውሀው ፍል ከመሆኑ የተነሳ የተለያዩ ምግቦችን ለማብሰያነትም ይገለገሉበታል፡፡ በተጨማሪም በአካባቢው ጥብቅ ደን
በመኖሩ ለፓርክነት ከሚጠኑ ቦታዎች አንዱ ነው፡፡ ይህ ደን በጋምቤላና በኢትዮ ሱዳን ድንበር ላይ ይገኛል፤ በደኑ ውስጥ ዝሆንና
ቀጭኔ ሲኖሩ በበጋ ሁሌ ሰደድ እሳት ስለሚከሰት ወደ ሱዳን በመሰደድ ክረምት ሲሆን እንደሚመለሱ በአካባቢው የሚኖሩ ሰዎች ይናገራሉ፡፡
3ኛ. ካዊ ሹመቴ ፓርክ፡-
ይህ ፓርክ በካዊ ሹመቴ ቀበሌ ውስጥ ሲገኝ ከቶንኮ በግምት በ25 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ይህ አካባቢ ለፓርክነት
አገልግሎት እንዲውል ጥበቃ እየተደረገለት ያለ ሲሆን በውስጡ አንበሳ፣ ጉሬዛ፣ ጎሽ፣ ጦጣ፣ ዝንጀሮ፣ ነብር፣ ሚዳቆ፣ እና የተለያዩ
ብርቅዬ የሆኑ የአእዋፍ ዝርያዎች መኖሪያም ነው፡፡
4ኛ. ሸሞሎ ተራራ፡-
በዋንጋጊተን ቀበሌ የሚገኘው ይህ ተራራ በግምት ከቶንጎ በ3 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ይህ መስህብ በተፈጥሮ እንደድንጋይ
ቀጥ ብሎ የቆመ ተራራ ነው፡፡ በላዩ ላይ ጥቃቅን እፅዋትና ቁጥቋጦዎች ሲገኙበት በማዕድን በተለይ በሜርኩሪና በወርቅ ማእድን የበለጸገ
እንደሆነ ይነገራል፡፡ አለት ሲሆን ወደ ተራራው መውጣትም ሆነ መውረድ አይቻልም፡፡ ሌሎች አነስተኛ ተራሮችም በዙሪያው ይገኛሉ፡፡
5ኛ. የንጉ ታሪካዊ ዋሻዎች፡-
የንጉ ቀበሌ ላይ የሚገኙት እነዚህ ዋሻዎች በቁጥር 3 ሲሆኑ ሁለቱ ግን ተቀራራቢ ናቸው ሁለት ሆነው በመካከላቸው ከ30-40
ሜትር ርቀት ሲኖር በፊት የኮሞ ብሔረሰብ ተወላጆች ከዛሬ 4 እና 5 ዓመት በፊት ድረስ እንደመኖሪያነት እና ከተለያዩ አደጋዎች
ለመከላከል እንደምሽግነት ይጠቀሙበት ነበር፡፡ አንዱ ተፈጥሮአዊ ሲሆን ከቶንጎ በ20 ኪ.ሜ ርቀት አካባቢ ይገኛል፡፡ በዙሪያው ጥብቅ
ደን ሲኖር በደኑ ውስጥም በካው ሹመቴ ደን ውስጥ የሚገኙት የዱር እንስሳት ሁሉ በዚህ ይኖራሉ፡፡
6ኛ. ሀሮ ዲማ ፏፋቴ፡-
ተፈጥሮአዊ ሲሆን በዋንጋጊተን ቀበሌ ይገኛል፡፡ ለመስኖ አገልግሎት ይውላል፡፡ በክረምት የውሀው መጠን ከፍተኛ ሲሆን
በበጋ ግን ለመስኖ ስለሚጠቀሙበት ውሀው ይቀንሳል፡፡ አካባቢው በጥብቅ ደን የተከበበ ነው፡፡
በማኦ ኮሞ ልዩ ወረዳ ውስጥ ከሚገኙት ሶስት ነባር ብሔረሰቦች ውስጥ አንዱ የኮሞ ብሔረሰብ ነው፡፡
የኮሞ ብሔረሰብ የጋብቻ ስርዓት
የኮሞ ብሄረሰብ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከሚገኙት 5 ነባር ብሄረሰቦች ውስጥ አንዱ ሲሆን በማኦ ኮሞ ልዩ ወረዳ የሚገኝ
ነው፡፡ ይህ ህዝብ የራሱ የሆነ ባህል፣ ታሪክ፣ ወግና ስርዓት አለው፡፡ በብሔረሰቡ የሚታወቁ አራት አይነት ጋብቻዎች አሉ፡፡ እነሱም
የስርቆሽ፣ የሽምግልና፣ የውርስ እና የለውጥ ጋብቻ ሲሆኑ ለዛሬ ከእነዚህ የጋብቻ ስርዓቶች ውስጥ አንዱን እናያለን፡፡
ከጋብቻ አይነቶች ውስጥ በጣም ታዋቂውና ተወዳጁ ወጣቶች እርስ በእርስ ተፈላልገውና ተፈቃቅረው የሚጋቡበት የስርቆሽ ጋብቻ
ነው፡፡ አሁን እየቀረ ቢመጣም በባህሉ የተለመደው የጋብቻ እድሜ ለሴት ልጅ እስከ 12 አመት ሲሆን ለወንድ ልጅ ደግሞ 14 አመት
ነበር፡፡ ከዚህ እድሜ በላይ ሳያገባ የዘለለ እድሜ ልኩን አያገባምና ቆሞ ቀር ይሆናል፡፡ ይህ በባህሉ ስላለ ወጣቶች ጊዜያቸውን
በአግባቡ ተጠቅመው በእድሜያቸው ለመጋባት ከፍተኛ የሆነ ጥረት ያደርጉ ነበር፡፡ በአሁኑ ሰዓት ግን ይህ የግንዛቤ ችግር በማህረሰቡ
ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ተቀርፏል ለማለት ይቻላል፡፡ ወጣቶች እድሜያቸውን በትምህርት ሰለሚያሳልፉ የሚያገቡበት የእድሜ ገደብ ከሃያ እስከ
ሰላሳዎቹ ውስጥ ገብቷል፡፡
በስርቆሽ ጋብቻ ጊዜ አንድ ወጣት በአንዲት ኮረዳ ፍቅር ከተጠመደ የቤተሰባቸውን ፍቃድ ሳይጠይቅ በወንዱ ጠያቂነት የሚፈፀም
ነው፡፡ ይህ ጋብቻ ዘመናዊ ጋብቻን የሚተካ ሲሆን ወንዱ ሴቷን በወንዝ፣ በእንጨት ለቀማ ቦታ ወይም የገበያ ቦታ ተከትሏት በመሄድ
ለብቻዋ ሲያገኛት ሎሜ ወይም ከረሜላ ይሰጣታል፡፡ መልዕክቱ አፈቅርሻለሁ ነው፡፡ ሴቷ የምትቀበል ከሆነች ፍቅሯን ገልፃለታለችና ፍቅራቸው
ይቀጥላል፡፡ እምቢ አልቀበልም የምትል ከሆነች እንደምንም አግባብቷት ሊሰጣት ይሞክራል፡፡ አሁንም እምቢ የምትል ከሆነች ክብሬን
ነካሽ ብሎ ሊተነኩሳት ይችላል፡፡ ነገር ግን እሷ ስትሽኮረመም እንደሆነ እንጂ ከልብ ላይሆን ይችላልና ተስፋ አይቆርጥም፡፡ በመጨረሻም
ታረጋጋውና ሎሚውን ትቀበለዋለች፡፡ ማፍቀሯ ተረጋገጠ ማለት ነው፡፡
ከተቀበለች በኋላ የመገናኛ ጊዜ ቀጠሮ ይይዙና ይለያያሉ፡፡ በሚገናኙበት ሰዓት ያው ፍቅር ነውና ተቃቅፈው የልባቸውን እያወሩ የወደፊት የትዳር ህይወት ምን መሆን እንደሚችል እየተነጋገሩ
በወንዝ ዳር ቁጭ ብለው የንፋሱን ሽውታ እና የወፎችን ፉጨት እየሰሙ መንፈሳቸውን እያረኩ ቀኑን ሙሉ ቆይተው ምሽት የቀጣይ መገናኛ
ቀጠሮ ይዘው ወደ ቤታቸው ተለያይተው ለመመለስ ሲፈልጉ መለያየት እየከበዳቸው በግድ ይለያዩና ወደየቤታቸው ይገባሉ፡፡
በተደጋጋሚ ቀጠሮ እየያዙ ሲገናኙ መቆየታቸው አንድ ነገር ይዞ እንደሚመጣ ልንገምት እንችላለን፡፡ ቤተሰብ ጋብቻን ይወቅልን
የሚለው አስተሳሰብ በኮሞ የስርቆሽ ጋብቻ ጊዜ አይታሰብም፡፡ በባህሉ የስርቆት ጋብቻ የተለመደ በመሆኑ በተወሰነ ደረጃ የልጅቷ ቤተሰቦች
ቢያዝኑም በልጁ ቤተሰቦች ዘንድ ፌሽታ ነው የሚሆነው፡፡ የተፋቀሩት ወደ ልጁ ቤት ከገቡ በኋላ የልጅቷ አባት ልጄን ደፍሯል በማለት
ወጣት አስልኮ ልጅቷ ወደቤቱ እንድትመለስ ያስደርጋል፡፡ ልጅቷ የልጁን ቤት ከመልቀቋ በፊት ወጣት አስልኮ የመመለስ ሁኔታ በባህሉ
ስላለና እንደሚገጥማቸው ስለሚያውቁ ቀድመው ዝግጅት አድርገውና ተመካክረው ለሊት ከቤተሰቦቿ ቤት ከጥበቃ አምልጣ ወጥታ የሚገናኙበትንና
ተያይዘው ወደ ልጁ ቤት የሚመለሱበትን ቦታና ሰዓት ይቀጣጠሩና ይልካታል፡፡ ምንም እንኳን ከቤታቸው ታስራ ልዩ ጥበቃ ቢደረግባትም
እንደምንም አምልጣ በቀጠሮው ቦታ ተገናኝተው ተያይዘው ወደ ልጁ ቤት ይገባሉ፡፡
በንጋታው እንደገና አባት ወጣት አስልኮ ያስወስዳታል፡፡ አሁንም አምልጣ ከልጁ ጋር ተመልሳ ወደ ቤቱ ትገባለች፡፡ በዚህ
ሂደት ውስጥ እንደተጋቡ አይቆጠርም የመፈተኛ ግዜ ስለሆነ፡፡ ለሶስተኛ ግዜ አባት ወጣት አስልኮ ያስወስዳታል፤ አሁንም ከልጁ አምልጣ
ከተመለሰች አባቷ እውነት ልጄ ልጁን ስለምታፈቅረው ነው ወደቤቱ ተመልሳ ጠፍታ የምትገባው ብሎ ጋብቻውን እንዲፀና መርቆ የልጁ እና
የልጅቷ ቤተሰብ ለቤተሰብ ዝምድና እንዲጠናከር ያደርጋል፡፡ ልጅቷ ግን በወጣቶች ወደ አባቷ ቤት ስትመለስ እንደምንም አምልጣ ካልሄደች
ስለማታፈቅረው ነው ተብሎ ጋብቻው አይፀናም፡፡
ጋብቻን የበለጠ ለማፅናት ቀጣዩ ሂደት ማጫ (እጅ መንሻን) አስመልክቶ ከልጁ ቤተሰብ ለልጅቷ ቤተሰብ የሚበረከተው ዶሮና
ሙክት ሲሆን ሙክቱ ሲታረድ የልጅቱ አባትና የልጁ አባት በደም ይጨባበጣሉ፡፡ ይህም የሚያመለክተው ልጅቷ ልጁን አትክደውም፤ ልጁ
ደግሞ ልጅቷን፤ የሚል የቃል ኪዳን ደም ነው፡፡ ሌላው የስጋ ማባያ ጨው፣ በርበሬ፣ ቅቤ እና ሌሎች ቅመሞች ተይዘው ወደልጅቷ ቤተሰብ
ቤት የልጁ አባት ከአስታራቂ ሽማግሌ ጋር ሆኖ ይዞ ይሄዳል፡፡ ዶሮ ወይም የታረደው ስጋ ተበልቶ በገንቦ የተወሰደ አረቄ ወይም ቦርዴ
ወይም ጠጅ ተጠጥቶ ይጨፈራል፡፡
ልጁ ወደ ልጅቷ ቤት ለትውውቅ ሲሄድ ሙክት ተይዞ ይሄዳል፡፡ በዛን ወቅት ለልጅቷ ቤተሰብ ጥሪ ተደርጎ ከቤታቸው ተገናኝተው
ይበላል ይጠጣል፡፡ ከተጠገበ በኋላ ለጅቷን ይዞ ሊወጣ ሲነሳ የዝምድና ማረጋገጫ እና የልጁን ትግስትና አስተዋይነት ለመፈተን እበት
ወይም ጭቃ ተወርውሮበት የማይናደድና አጸፋውን የማይመልስ ከሆነ ታጋሽና አስተዋይ ነው ተብሎ የበዛ ክብር ይቸረዋል፡፡ የሚነጫነጭና
አፀፋ ለመመለስ የሚሞክር ከሆነ ነጭናጫ ነው ተብሎ ይናቃል፡፡
በአሁኑ ሰዓት ማጫ ወይም እጅ መንሻ ይሰጥ የነበረው ወደ ብር ተቀይሯል፡፡ ይህም የእጅ መንሻ ተብሎ ለአባቷ ከ2000-3000
ብር ድረስ ይሰጣል፡፡ ወደ ጋብቻ ገብተው ለመጀመሪየ ግዜ ልጁ ልጅቷ ሲገናኛት ክብረ ንፅህና ካላት የልጁ አባት ለልጅቷ ፍየል ወይም
መቋቋሚያ ብር ይሸልማታል፡፡ ክብረ ንፅህና ከሌላት ከማን እንዳጠፋች ተጠይቃ ገልፃ ልጁ
ፍየል ለልጅቷ እና ለሽማግሌዎች ተቀጥቶ የልጅቷ መቋቋሚያ ሲሆናት አስታራቂ ሽማግሌዎች የራሳቸውን ከዛ አርደው ይበሉታል፡፡
የወረዳው የኢንቨስትመንት አማራጮች
ከአሶሳ ወረዳ እስከ ሱዳን ቦርደርን አካቶ የወረደውን ሰሜን ምዕራብ ጀምሮ እስከ ደቡብ የሚያዋስን ነው፡፡ መሬቱ ሙሉ
በሙሉ ቆላ ነው፡፡ ከ32 ቀበሌያት ስድስቱ ብቻ ወይና ደጋ ሆነው 26 ቆላ ናቸው፡፡ ለኢንቨስትመንት አመቺ የሆነው ደግሞ ቆላ ውስጥ
ነው፡፡ ሰፊ ክረምት ከበጋ የሚፈሱ ወንዞች አሉ፡፡ ዳጉስ ወንዝ እስከዳካር የሚሄደው፣ ዳካ ወንዝ፣ በመሀል ትናንሽ ወንዞች አሉ፡፡
ሠሊጥ፣ ኑግ፣ አኩሪ አተር፣ ኮረሪማ፣ ዝንጅብል፣ ማንጎ፣ ብርቱካን፣ ሙዝ፣ መንደሪን በብዛት ይመረታሉ፡፡ ማንጎና ብርቱካን
ምርት በሰፊው መኖሩ እያሸጉ ለማቅረብ ጥሩ አማራጭ ነው፡፡ ቡና በስድስቱ ወይና ደጋ ቀበሌያት ላይ ይገኛል፤ ቆላ ላይ በመስኖ መደገፍ
ይፈልጋል፡፡ የንብ እርባታ ቆላው ላይ ባህላዊ መንገድ በሰፊው ሲኖር በዘመናዊ መንገድ በጃፓን ኤምባሲ በተደረገ እርዳታ ሙከራ ተደርጓል፡፡
ወደ ወረዳው በመምጣት ኢንቨስት ለማድረግ ለሚፈልግ በአንደኛ ደረጃ ተመራጭ ነው በስድስት ወር በአንድ ዓመት ምርት የሚሰበሰብበት
ተመራጭ መንገድ ነው፡፡እጣን ከቶንጎ 50 ኪ.ሜ አካባቢ በንጋ የሚባል ቀበሌ ላይ አንድ ኢንቨስተር ብቻ እየሰራ ይገኛል፤ ተጨማሪ ሌላ አቅጣጫም ጠይቀው ተሰጥቷቸዋል፡፡ ሌሎች ኢንቨስተሮችም በመምጣትው ቢያለሙ ተጠቃሚ መሆን ይችላሉ፡፡
በወረዳው በ2006 የተሰበሰበ የምርት መጠን፣ ሰሊጥ 4085 በኩንታል፣ በቆሎ 57964 በኩንታል፣ ማሽላ 84306 በኩንታል፣ ጤፍ 2574 በኩንታል፣ ዳጉሳ 1044፣ ስንዴ 3681፣ ገብስ 1285፣ ባቄላ 1033፣ ቦሎቄ 11286፣ አኩሪ አተር 1486፣ ኑግ 7710፣ ተልባ 274፣ ለውዝ 2425፣ ጎመን ዘር 285፤ በፍራፍሬ ደግሞ ማንጎ 2507፣ ፓፓያ 427፣ ሙዝ 1728፣ ብርቱካን 1275፣ በጫት ምርት 3387፣ ቡና 1326 የቡና ምርት ባለፈው ዓመት ትንሽ ነበር አሁን ግን በሰፊው ይዟል፤ ይህ የሚያሳየን ወረዳው ለኢንቨስትመንት ምቹ መሆኗንና በተለያየ መስክ ወደ ወረዳው በመሄድ ኢንቨስት ማድረግ እንደሚቻል ነው፡፡
No comments:
Post a Comment