አሁን አየ ዓይኔ
የቱሪዝም ንግድ ትርኢት በአዲስ አበባ
የሃገራችን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ
ለዘመናት ይጓዝበት ከነበረው ከርፋፋና ቀርፋፋ አካሄድ ወጥቶ ያለፍትን ጥቂት ዓመታት ሶምሶማ ወደሚባል ፍጥነት እየገባ መጥቷል፡፡
የሁልም ጊዜም ቁጭታችን ባለን ነገር ባለመጠቀም ከሌላቸው ህዝቦች ውራ ቁጥር መግባታችን ነበር፡፡ ስለአለን ነገር እንኳን ስናስብ
ከሌላው የምንልቅበት በርካታ ነገር አለ፤ እኛ ያለን ሃብት እውቀት ገንዘብና ቴክኖሎጂ ሊያመጡት አይችሉም፤ ብዝኃ- ህይወትን ከባህል
ጋር፣ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሮአዊ ሃብቶችን ታድለናል፡፡ ለጥቁር ህዝብ ተምሳሌት የሚሆን ትናንትና ያለን ህዝቦች ነን፤ ይህንን ተጠቅመን
መጠቀም አቅቶን ኑሯል፤ እንደውም አናወራውም ስለራስ ማውራት መታበይ ነው የሚል ብሂል አለን፤ ስለራስ ካልተወራ ውጤት የማይገኝበት
የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ልባችንን የምናሳርፍበት አልሆን ያለውም ለዚህ ነው፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ስለራሳችን
ማውራት ጀምረናል፤ ስለነገርናቸው አምነው ብዙዎች እየመጡ ነው…. እራስን መሸጥ ላይ የነበሩብንን ውስንነቶች ለመቅረፍ እያደረግንው
ያለው ጥረት እያመጣ ያለው ውጤት ይበልጥ የሚያተጋ እንደሆነ ተመልክተናል፡፡ ሌላውን ትተን ባለፍት አስር ዓመታት ብቻ ይህቺ ሃገር
የጉባኤ መዳረሻ/conference tourism/ ማእከል በመሆን አያሌ ጉባኤዎችን አስተናግዳለች፤ የመዲናዋ ሆቴሎች በየቀኑ መዋለድ
ሚስጥርም ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡
እንደሌላው ዓለም ሊያውም በላቀ
የባህል፣የታሪክና የተፈጥሮ ሃብችን ታድለናል፤ ቱሪዝም በየግዜው ከሚያድግ ቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መስፋፋት ጋር የሚፈልገው
እነኚህን ዋንኛ ጉዳዮች ነው፡፡ ግን በየዓመቱ ብልጫ ያለው ጎብኚን ለመሳብ የማስተዋወቅ ስራዎች ወሳኝ ናቸው፤ የሌላው ዓለም የማስተዋወቅ
ስራ በመንግስት ጫንቃ ላይ የወደቀ አይደለም የባለሃብቱ ተሳትፎ አለበት፤ አሁንም ቢሆን የኛ ቱሪዝም ገንዘብ መሆን ካለበት ባለሃብቱ
ሃገሪቱን በማስተዋወቅ በኩል እኩል ድርሻ ኖሮት በባለቤትነት ሊሰራ ይገባል፡፡
ሰሞኑን መዲናችን አንድ የቱሪዝም
ንግድ ትርኢት በኤግዚቢሽን ማእከል እያስተናገደች ነው፡፡ ትርኢቱ የመጀመሪያው ሲሆን ምናልባትም የንግዱ ህብረተሰብ ፊቱን ወዴት
እያዞረ የሚያሳይ ሳይሆን አይቀርም በሚል ለቱሪዝማችን ሶምሶማ ሩጫ የበለጠ ፍጥነት የሚመኙም አሉ፡፡ በሌላ በኩል ንግድ ትርኢቱ
ከግብርና ንግድ ትርኢት ጋር አብሮ መሆኑ ለአረንጓዴ ቱሪዝም ልማት በእጅጉ መነቃቃትን ይፈጥራል፡፡
በሃገር ውስጥ ይህንን መሰል የቱሪዝም
ንግድ ትርኢት መካሄዳቸው ከሌሎች ተግባራት ጋር ተዳምረው ስናያቸው ውጤታቸው ሩቅ አይሆንም የሚል እምነት አለን፤ ከዚህ በፊት በውጪው
ዓለም በሚደረጉ የንግድ ትርኢቶች ላይ የአንበሳውን ድርሻ ይይዝ የነበረው የፌዴራል ባህል ቱሪዝም ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ነበር፤
ይህ ደግሞ ውጤቱ የልብ አያደርስም፤ አንድም ህዝባዊ መሰረት አይኖረውም፤ አንድም ዘላቂነቱ ዋስትና የለውም፤ አሁን አሁን ግን ከዚህ
የተለዩ ስልቶችን መከተል ጀምረናል፡፡ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፍ የማስተዋወቅና መስህብ የማልማት ተግባራት ተጀምረዋል፡፡ ባለፍት
ሁለት የበርሊን ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢቶች ላይ ክልሎች እንዲሳተፍ ተደርጓል፡፡ እንደውም በዘንድሮው የበርሊን ንግድ ትርኢት
ላይ እራሳቸውን በመሸጡ ረገድ ክልሎች ያደረጉት ተሳትፎ የሚበረታታ ነው፡፡ የሰሞኑን ዓይነት የቱሪዝም ንግድ ትርኢቶች በሃገር ቤት
መካሄዳቸው ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ የምናደርገውን ውድድር ያጠነክሩታል፡፡
ይህቺ ሃገር ሃገሬ ናት የሚል ሁሉ
ስለ መልካም ገጽታዋ፤ ስለ ክብሯ፤ እንዲሁም እንደ ዜጋ ስለ አምባሳደርነቱ ሊያስተዋውቃት ይገባል፡፡ ከቱሪዝም ልማት ተጠቃሚ ለሚሆኑ
አካላት ሁሉ ደግሞ ይህ ሃላፊነት እጥፍ ይሆናል፡፡ ሃላፊነት የሚሰማው የቱሪዝም ኢንቨስትመንት ማስፋፋት ይገባናል፡፡ ሃገሪቷን ለማስተዋወቅ
ገሸሽ እያሉ ጥቅሙን ለመካፈል መሻማቱ የትም አያደርስም፡፡ ለአብነት ያክል
ሁለት ስኬታማ ተግባራትን እናንሳ ጎንደር ከተማ ላይ ሁሉም የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ባለድርሻ አካላት አንድ መማክርት አዋቅረዋል
እርሱም የጎንደር ከተማ የቱሪዝምና ባህል ገቢ አመንጪ ካውንስል፡፡ ይህ ካውንስል ገቢ ይፈልጋል፤ መስህቦችን ያለማል፤ የማስተዋወቅ
ስራዎችን ይሰራል፤ እንደዚሁ ሁሉ ስኬታማ የሚባለው የቢሸፍቱ ሆቴል ማኅበርም ልምድ በመለዋወጥ የአገልግሎት ጥራትን በማሳደግ እና
በማስተዋወቅ ስራዎች በኢንዱስትሪውና በባለሃብቱ መካከል ትስስር ከተፈጠረ ሊመጣ የሚችለውን ውጤት ከምናይባቸውም መካከል የሚጠቀሱ
ናቸው፡፡
አሁን አንድ ነገር ለማየት ችለናል….አዲስ
አበባ ላይ የከተመው የቱሪዝም የንግድ ትርኢት ነገ ብዙ ተሳታፊዎችን ወልዶ እራሱን ችሎ በመቀጠል በውጪው ዓለም የምናደርገውን ተሳትፎ
የሚያሳድግና ከፍተኛ መነቃቃትን የሚፈጥር በመሆኑ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡
No comments:
Post a Comment