Monday, June 4, 2012


ሰኔ ሰላሳ የሚያሳድዳቸው የባህል ፌስቲቫሎች

ደማቁ የእሬቻ በዓል
ይሄ ሰኔ ሰላሳ የሰነፍ ተማሪ  የምጥ ቀን ነበር…አሁን አሁን ተቋማት.. በጀት ዓመታቸውን ለመጨረስ…ከፋይዳው ይልቅ ለሪፖርት የሚሆን ተግባር ለማከናወን ተገልጦ የሚታይ ጉድ እየተመለከትን ነው፡፡ የባህል ፌስቲቫሎች በባህል ልማት በቱሪዝም ምርትነትና በገጽታ ግንባታ፤ የሚኖራቸው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ይህንንም በእጅጉ እናበረታታለን፤ ከዳር ዳር የባህል ፌስቲቫሎች እንዲናኙ ምኞት ብቻ ሳይሆን ይፈጸም ዘንድ እንተጋለን፤ግን እንዴት ? ዓላማስ አለው ወይ…ግቡስ ምንድን ነው እነዚህን ሁሉ ጥያቄዎች ሊመልስ ይገባዋል፡፡


የጋሞ ጎፋ፣ወላይታና ሃድያ መስቀል በባህል ፌስቲቫል ደረጃ ትኩረት ሰጥተው ያከብሩታል…ሰኔ ሰላሳ ሲደርስም የሚያወርዱት ዱብ እዳ የለም፤ ለምሳሌ ይህ ስልት የተሳካለቸውና አርአያ ሊባሉ የሚችሉትን እናንሳ፤ ሲዳማ ፍቼን ያከብራል፤ ትኩረት ሰጥቶ ደግሶ….በእቅድ በተመራ ሁኔታ የቱሪስት መስህብ እያደረገው ይገኛል፤ ጎንደር ጥምቀትን ቢሸፍቱ እሬቻን በማስታከክ የሚያዘጋጁት የባህል ፌስቲቫል በእጅጉ እየዳበረ የመጣ መልክ ያለው፤በእቅድ የሚመራ፤እንደአስፈላጊነቱ የማይቀያየር ነው፡፡ ስልጤዎች አረፋን አስታከው ባህላዊ እሴቶቻቸውን ማስተዋወቅ ጀምረዋል፡፡ እነዚህ እንደ ምሳሌ ያነሳናቸው የባህል ፌስቲቫሎች ለጎብኚ የተመቸ መርሃ-ግብር ያላቸው፣በየጊዜው እየዳበሩ የመጡ፣እቅድን ለማሳካት ብቻ ሳይሆን ለአያሌ ትርፎች የሚሰሩ ክንዋኔዎች ናቸው፡፡

ስም ባንጠቅስም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዓመታዊ እቅድና ትግበራን በመገምገም ሂደት አንዱ ከሌላው ያለውን ልዩነት ለማስተካከል ሲባል ፈጸምን ለማለት የሚደረጉ ዱብ እዳ የባህል ፌስቲቫሎች ተበራክተዋል፤ ክልል አቀፍ፣ዞናዊና ከተማ አቀፍ የባህል ፌስቲቫሎች የበጀት ዓመቱ ሊጠናቀቅ ቀናት ሲቀሩ ከሰኔ ሰላሳ ጋር ግብ ግብ ገጥሞ፣ወረዳዎችን ድንገት በመጥራት ተከናውኖ ነበር ለማለት የሚደረጉ ዝግጅቶች ተበራክተዋል፡፡

የባህል ፌስቲቫል ማዘጋጀት መቻል ከብዙ አቅጣጫ ጠቀሜታዎች ያሉት ተግባር ቢሆንም እቅድን ለማሳካት እና ተደረገ የሚሉ የመገናኛ ብዙሃን ሽፋኖችን ለማግኘት ብቻ ከሆነ ግን በትውልድ ሥነ-ልቦና እና በሃገር ሃብት ላይ ማፌዝ ይሆናል፡፡ የዚህ ችግር ምልክቶች መታየት ጀምረዋል፡፡ የባህል ፌስቲቫል ማለት ከዘውጉ አንዱን ማለትም የባህል ኪነትን ብቻ ያካተተ እስኪመስል ጨፍረው የሚበተኑ አስጨፍረው የሚበትኑ ተበራክተዋል፡፡

በዘርፍ በጎ ጅምር ካላቸው ምርጥ ተሞክሮን በመቅሰም ያንን በመቀመር እቅድ የሚመራው እየበሰለ እና እያደገ የሚሄድ መልክ ያለው ዓላማውን ስለማሳካቱ ሊገመገምና ሊቆጠር የሚችል ውጤት የሚያስመዘግብ ዝግጅት ለማዘጋጀት መሰራት ይኖርበታል፤ መገናኛ ብዙሃን  ይህን መሰሉን ዝግጅት ሽፋን ሲሰጡ ከፋይዳ አንጻር ሊመለከቱ የሚችሉበት ዓይን ሊኖራቸው ይገባል….አብረን ብንጮህ ትርጉም የለውም….ግን ምንም ውጤት ለማይኖረው ሁላችንንም ይደክመናል፡፡   

No comments:

Post a Comment