ዜና
የአዊ የፈረስ ትርኢት-ለቱሪዝም
ዜና-ሀገሬ ሚዲያ
አዊ ባንጃ ወረዳ awi festival |
ፈረስ ለአዊ ሁለንተናው ነው….ለእርሻ ስራው ጉልበቱ በመሆኑ ይወደዋል….በክፉም ሆነ በደግ በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች መጓጓዣ ትራንስፖርቱ ነውና ሁሌም ያስፈልገዋል….አዊ በደስታውም ቢሆን በዓሉን የሚያደምቀው በፈረስ ነው….ሰርጉ ጭምር በፈረስ ይዋባል፤ሞቶ ወደ መቃብር ሲሸኝም ፈረስ መሸኛው ነው…..
በ1933 ዓ.ም በመሰባሰብ አብሮነትን በተደራጀ መልኩ አንድ ያለው የአዊ ፈረሰኞች ማኅበር ዘንድሮ 71ኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ የአዊ ፈረሰኞች ማኅበር ጠላትን ከሃገር ለማስወጣት አንድነትን ለመፍጠር በሚል በአንድ የተደራጀ ነበር ያኔ….. ዛሬ ደግሞ የአዊን እሴት ለማስተዋወቅ በአንድ ያበረ አንድ ህብረት ሆኗል፡፡
አቶ አቡኑ ይግረም ይባላሉ የወቅቱ የአዊ ፈረሰኞች ማኅበር ሊቀ-መንበር፤22,275 አባላት ያሉት ይህ ማኀበር በየዓመቱ ዓመታዊ በዓል ያከብራል፤ይህ በዓል የአዊ ፈረሰኞች ቀን ይባላል፡፡ በዚህ የባህል አከባበር ደንብ አመታዊው በዓል ከወረዳ ወደ ወረዳ እየተዘዋወረ የሚከበር ነው፡፡ አዊ ዞን አስር ወረዳዎች አሉት፤አንድ ወረዳ በአስር አመት አንዴ የአዊ ፈረሰኞች ቀንን የማዘጋጀት እድል ይገጥመዋል፡፡
በዚህ የፈረሰኞች ቀን ከፈረስ ስፖርት ጋር ተያያዥነት ያላቸው ባህላዊ ስፖርቶች ይካሄዳሉ፡፡ እነዚህ ባህላዊ የፈረስ ስፖርቶች በዋናነት ሶስት ናቸው፤ከእነዚህ መካከል ጉግስና ሽርጥ ቀልብ ሳቢ ውድድሮች ናቸው፡፡ በውድድር መልኩ ከሚዘጋጁት ውድድሮች ባሻገር በፈረስ የሚደረጉት ያልተደራጁ ትርኢቶች በራሳቸው ማራኪና ሳቢ ናቸው፡፡ እያንዳንዱ ወረዳ በዚህ አመታዊ የፈረስ ትርኢት ላይ አንድ አንድ ከብት ይዞ ይመጣል፤ በትንሹ በበዓሉ አስር ከብቶች ይታረዳሉ፡፡
የአዊ የፈረሰኞች ቀን በሚል በየዓመቱ የሚከበረው ይህ የፈረስ ትርኢት በወርሃ ጥር ካሉት በአንዱ እሁድ ቀን ይከበራል፤ መደበኛ ቀን የለውም ወሩ ግን የግድ ጥር ዕለቱም እሁድ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ከዚህ ባሻገር ዓመታዊው በዓል መቼ እንደሚውል በማኅበሩ ይገለጻል፡፡ የዘንድሮው በዓል ጥር 20 ቀን 2004 ዓ.ም በደማቅ ዝግጅት ተከብሯል፡፡ በድምቀት እና እንግዳን በማሳተፍ ደረጃ የመጀመሪያ ነው የተባለለት የዘንድሮውን በዓል ያስተናገደችው ቲሊሊ ነበረች፡፡
ይህን ማራኪ ውድድር ወደ ቱሪዝም ምርት ለመቀየር ቢአርሲ የተባለ የግል በቱሪዝም እና በማስጎብኘት ስራ የተሰማራ ድርጅት እንቅስቃሴ ጀምሯል የዘንድሮ በዓል እንዲደምቅ ካደረጉት እድሎች መካከል የቢአርሲ አጋር መሆን ነው ይላሉ በቢአርሲ የባህር ዳር ፕሮጀክት ማናጀርና የአዊ ፈረስ ፌስቲቫል ድርጅቱን በመወከል አስተባባሪ የነበሩት አቶ ማሩ ኑሩ፤
ቢአር ሲ ይህን የአዊ የፈረስ ፌስቲቫል ከሰባት አስርት አመት በላይ ያደረገው ጉዞ ብቻውን የእሴቱን መዳበር የሚያሳይ መሆኑን በመጥቀስ በዩኔስኮ ጭምር ባህሉ እንዲመዘገብ ጥረት ለማድረግ ማቀዳቸውን ገልጸዋል፡፡ እንደውም የአዊ ፈረሰኞች ማኅበርን የዓለም አቀፍ ፈረሰኞች ማኅበር አባል ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመራቸውን አቶ ማሩ ገልጸውልናል፡፡
የአዊ ፈረሰኞች የፈረስ ትርኢት በዓል ቢያንስ በአምስት ዓመት አንዴ በሃገር አቀፍ ደረጃ በሚፈጠር ንቅናቄ እንዲከበር መታሰቡን ለመረዳት ችለናል፡፡
No comments:
Post a Comment