የኢማም ሱጋቶ መኖሪያ ቤት…..
ወራቤ የስልጤ ዞን ርእሰ ከተማ ናት፡፡ ስልጤ ዞን በስራ ወዳድነታቸው የሚታወቁት የስልጤ ብሄረሰብ ምድር ነው፡፡ 2537.50 ኪ.ሜትር ስኩዌር የሚሰፋው የስልጤ ዞን ከ950.000 በላይ ህዝብ ይኖርበታል፡፡
ምእራብ አዘርነት በርበሬ ወረዳ በስልጤ ዞን ከሚገኙ 8 ወረዳዎች አንዱ ነው፤ይህ ወረዳ ከዞኑ መዲና ከወራቤ 83 ኪ.ሜትር ገደማ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ሌራ የምእራብ አዘርነት በርበሬ ወረዳ ማእከል ከተማ ናት፡፡ በወረዳው በርካታ ተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽ መስህቦች ይገኛሉ፡፡ በአጭሩ የኢማም ሱጋቶ ታሪካዊ ቤትን እንቃኝ…..
silta zone attraction |
ኢማም ሱጋቶ የዛሬ መቶ ዓመት ገደማ ስልጤንና አካባቢውን ጎጎት የሚባል አደረጃጀት በመፍጠር ያስተዳድሩ የነበሩ በሳል መሪ ነበሩ፤ ከእኒህ መሪ ታሪክ ጀርባ ብዙ ያልተወራላቸው የጀብድ ታሪኮች እንዳሉ በአፍ ከሚወረሱ የአበው የታሪክ ሽግግሮች ለመረዳት ይቻላል፡፡
ኢማም ሱጋቶ ዘይኔ በአካባቢው ላይ የሚቃጡ ግጭቶችንና ጥቃቶችን በመመከት በጦረኝነታቸው የሚታወቁ ጀግና መሪ ናቸው፤ስልጤዎች ይህንን ጀግንነት አድንቀው ለኢማም ሱጋቶ አዚመዋል፣ተቀኝተዋል፡፡ ከጀብድ ተግባራቸው ጋር አብሮ ለሚነሳው ፈረሳቸው ጭምርም ቅኔ ቀርቦለታል፡፡
ኢማም ሱጋቶ ዘይኔ ከስልጤ አካባቢዎች በአለፈ ሃላባ እና ሃድያ ጭምር ያስተዳድሩ እንጂ እንደ መናገሻ ማእከላቸው ሆኖ ያገለገለውን የሚያምረውን መኖሪያ ቤታቸውን ያነጹት በምእራብ አዘርነት በርበሬ ወረዳ ነው፡፡
ባለ ፎቁ የኢማም ሱጋቶ መኖሪያ ቤት ከሌራ ከተማ 4 ኪ.ሜትር ርቀት ላይ ልዩ ስሙ ዱና ከሚባለው ስፍራ ይገኛል፡፡ በተዋበ አረንጓዴ ዙሪያ ገባ ተጅቦ ያረፈው ይህ ባለ አንድ ፎቅ ህንጻ ቤት በዙሪያው ያሉ እድሜ ጠገብ ዛፎች አሳምረውታል፡፡ የቤቱ አሰራር ከጅማው አባ ጅፋር ቤተ መንግስት አስተናነጽ ጋር መመሳሰል ይታይበታል፡፡
ይህ አንድ ምእት ዓመት እድሜን ያስቆጠረው ቅርስ የስልጤዎች ብቻ እሴት ሳይሆን የሃገርም ቅርስ ነው፡፡ ከቤቱ ጀርባ የቤት አሰራሩ ጥበብ ከዚያም ሲያልፍ የኢማሙ ሱጋቶ የጀግንነት ታሪኮችና ታሪኮቹ የፈጠሩት ሥነ-ቃል አንዱን መስህብ ብዙ ያደርገዋል፡፡
No comments:
Post a Comment