የትግራይ የባህል ፌስቲቫል በአክሱም ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡
በሜሮን ታምሩ
በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከሚገኙ 53 ወረዳዎች ውስጥ 34ቱ ወረዳዎች የተሳተፉበት ክልል አቀፍ የባህል ሳምንት
በስልጣኔ ፈር ቀዳጅ በሆነችው በአክሱም ከተማ በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ የባህል ማዕከል ከትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የባህል ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር ያዘጋጀውና ለ12 ግዜ እየተካሄደ የሚገኘው ክልል አቀፍ የባህል ሳምንት ባህላችን
ለሰላምና ለልማት በሚል መሪ ቃል ከግንቦት 17 እስከ ግንቦት 22 ቀን 2010 ዓ.ም. የሚቆይ ነው፡፡
በኩነቱ መክፈቻ ዕለት ከማለዳው ጀምሮ ከ34 ወረዳዎች የመጡት የባህል ቡድኖች በባህላዊ አልባሳታቸው በአጋጊያጣቸው በፀጉር
አሰራራቸው እንዲሁም በባህላዊ ውዝዋዜያቸውና በባህላዊ ክዋኔዎቻቸው አሸብርቀው በአክሱም ከተማ ጎዳናዎች ላይ በመዘዋወር ለከተማዋ
ህዝብ ባህላቸውን በማሳየት አክሱምን አድምቀዋት አርፍደዋል፡፡
በኩነቱ መክፈቻ ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የባህል ማዕከል
ዳይሬክተር ዶክተር እልፍነሽ ሀይሌ የክልሉ የባህልና የቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳዊት ሀይሉ ከክልሉና ከፌደራል የባህልና ቱሪዝም
ተቋማት የመጡ የሥራ ኃላፊዎች የክልሉና የከተማው ነዋሪዎች፣ የባህል ቡድኖችና ጥሪ የተደረገላቸው
እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
የትግራይ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳዊት ሀይሉ በእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ኩነቱን ያስጀመሩ ሲሆን በመክፈቻ
ንግግራቸውም በዚህ የባህል ሳምንት ሲወረድ ሲዋረድ የመጣውን የክልሉን ባህል ጠብቆ በማቆየት መተሳሰብና እና መፈቃቀር ለማጎልበት
ትልቅ ሚና እንዳለው ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የባህል ማዕከል ዳይሬክተር ዶክተር እልፍነሽ ኃይሌ በበኩላቸው ይህን በዓል
ማክበሩ ህዝቦች ለዘመናት ይዘውት የቆዩትን የአብሮነት የመቻቻል ፍቅርና መተሳሰብ በማጠናከር ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍ፣ ባህል ለልማትና
ለሰላም ያለውን ፋይዳ አጉልቶ በማውጣት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፓለቲካዊ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት
በሚደረግ ርብርብ የባህሉ ባለቤት ህዝብና ሁሉም በየደረጃው በኃላፊነት ሲንቀሳቀስ በባህሉ የሚኮራ ትውልድ መፍጠርና መገንባት ሲቻል
በመሆኑ በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ሳንወሰን ለዘርፉ እድገት የድርሻችንን እንድንወጣ እና ለባህል ልማትና እድገት ቀጣይነት ባለው መልኩ
ሁሉም እንዲረባረብ ጠይቀዋል፡፡
ባህላዊ ኩነቱ በቆይታው ከየወረዳዎቹ የመጡት
የባህል ቡድኖች የሚወዳደሩበት ባህላዊ እሴቶቻቸውን ከውዝዋዜያቸው ጋር አቀናጅተው የሚያቀረቡበት እንዲሁም ባህላዊ ትውፊቶች ላይ
ያተኮሩ ተውኔቶችና የተለያዩ መልዕክቶች የሚያስተላልፉ ግጥሞች፣ የሥነ ስዕልና የቅርጻ-ቅርፅ ውድድሮች ለታዳሚዎች እየቀረቡ የተካሄደ ሲሆን ነገ በሚካሄው የማጠናቀቂያ ሥነ-ሥርዓት ለአሸናፊዎች ባህላዊ ሽልማቶችን በመሸለም
በዓሉ ፍጻሜውን ያገኛል፡፡
ይህ የባህል ሳምንት ባህላዊ ስራዎች የቀረቡበት አውደ ርዕይን ያካተተ ሲሆን በአውደ ርዕዩ ላይ ባህላዊ የዕደ-ጥበብ ስራዎች እንዲሁም የሥነ ስዕል ውጤቶችና ሌሎች ባህልን የሚገልፁ
ስራዎች ለእይታ ቀርበዋል፡፡ በዚህ አውደ ራዕይ ከክልሉ ተሳታፊዎች ባሻገር ከጋምቤላ ክልልና ከአማራ ክልል የመጡ ተሳታዎች ስራዎቻቸውን
ይዘው ቀርበዋል፡፡
No comments:
Post a Comment