Thursday, October 20, 2016



አዲሱ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ብራንድ እና ቀጣዩ የመገናኛ ብዙኃን ሚና

=====================================
ኢትዮጵያ የመለዮ ስያሜውን LAND OF ORIGINS ያደረገ አዲስ የቱሪዝም አርማ እና መለዮ ስያሜ ይፋ አድርጋለች፡፡ በቅርቡ በኢትዮጵያ ቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት ጉባኤ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይፋ ያደረጉት አዲሱ የመለዮ ስያሜ ግማሽ ምዕተ ዓመት ያክል የአስራ ሦስት ወር ጸጋ በሚል ሲያገለግል የኖረውን ብራንድ ስያሜ የሚተካ ነው፡፡


በዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ሀገራችን በዓለም የቱሪዝም ገበያ ልክ ልትወዳደር በምትችልበት አግባብ የተቀረጸው አዲሱ የመለዮ ስያሜ ከዚህ በፊት ኢትዮጵያን ወክሎ የነበረውን የአስራ ሦስት ወር ብቸኛ ባለቤትነት ጨምሮ የሰው ልጅ፣ የረዥሙ ግዮን ወንዝ፣ የቡና፣ የአብረሃም እምነቶች ቀዳሚነት፣ የእጽዋት እና የአእዋፋት፣ የብርቅዬ ዱር እንስሳት፣ ለነጻነት የተደረገን ተጋድሎና የጥቁር ህዝቦች ታሪካዊ ድል የሌሎች በርካታ ቀዳሚነትን የሚወክሉ መገለጫዎች ሆኖ የቀረበ ነው፡፡
በአሰራሩ በሂደቱ እና ለምን አስፈለገ በሚለው ጥያቄዎች ዙሪያ ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ጥቅምት ስምንት ቀን 2009 ዓ.ም. ጠዋት የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት በካፒታል ሆቴል ከመገናኛ ብዙሃን ጋር መክሮ ነበር፡፡ የድርጅቱ የስራ ኃላፊዎች የብራንዱን እውን መሆን በተመለከተ ያለፈባቸውን ሂደቶች አስረድተዋል፡፡ ከቀድሞው የመለዮ ስያ የሚለይባቸውን ነጥቦች እና አዲሱን ብራንድ ለማሰራት የተደረጉትን ጥንቃቄዎች በስፋት ያስረዱ ሲሆን ኢትዮጵያ በአዲሱ ብራንድ ስያሜዋ ለዓለም ጎብኚዎች የምትገባውን ቃል ኪዳን እውን ለማድረግ እና ነን ያልንውን ሆነን እንድንገኝ መገናኛ ብዙሃን የበኩላቸውን እንዲወጡ ከድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ከአቶ ሰለሞን ታደሰ ጥሪ ቀርቧል፡፡
በመድረኩ በተለይም አማርኛ ስያሜ ከወዲሁ ትኩረት ተችሮት እንዲሰጠው የቀረበው ጥያቄ እና የብራንዱን ወጥነት በተመለከተ በሚሰሩ ስራዎች ላይ ጥንቃቄ እንዲደረግ በሚል ለቀረቡት ጥያቄዎች በአጭር ጊዜ ምላሽ እንደሚያገኙም ነው የተገለጸው፡፡
አዲሱ የኢትዮጵያ የመለዮ ስያሜ በዓለም ባንክ ድጋፍ በኢትዮጵያ ዘላቂ የቱሪዝም ልማት ፕሮጀክት አማካይነት ደቡብ አፍሪካ ተቀማጭነቱን ባደረገ ዓለም አቀፍ ተቋም መሰራቱን ለማወቅ ችለናል፡፡

No comments:

Post a Comment