Saturday, April 25, 2015



ባሌ ዞን
የባሌ ዞን በኦሮምያ ክልል ከሚገኙ ዞኖች አንዱ ሲሆን በቆዳ ስፋቱም ሁለተኛው  ነው፤ በስተምስራቅ የሶማሊያ ክልል፣ በሰሜናዊ ምስራቅ ምስራቅ ሐረርጌ፣ በሰሜን ምዕራብ ሐረርጌና አርሲ ዞን፣ በምዕራብ ምዕራብ አርሲ እና በደቡብ ጉጂ ዞን ያዋስኑታል፡፡ ዞኑ 14.93 በመቶ በደጋ፣ 21.54 በመቶ በወይናደጋ እና 63.53 በመቶ በቆላ የአየር ንብረት የተከፋፈለ ነው፡፡ መልከዓ ምድራዊ አቀማመጡም 55.89 በመቶ ሜዳማ፣ 30.7 በመቶ ወጣ ገባማ፣ 12.14 በመቶ ተራራማ እና ቀሪው 0.4 በመቶ ሸለቆማ ነው፡፡ በሀገራችን የቱሪዝም መስህቦች አንጋፋውን ስፍራ ከሚይዙ አካባቢዎች አንዱ የሆነው የባሌ ዞን እጅግ በርካታ የሆኑ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችን የታደለ ምድር ነው፡፡ ጥቂቶችን በዚህ ዕትም እንዳስሳለን፡፡


Friday, April 24, 2015



አርኪዎሎጂ
የሰው ዘር መገኛነታችንን ዳግም ያረጋገጠው ግኝት
ኢትዮጵያ ቀደምት የሰው ዘር መገኛ መሆኗን ያረጋገጡ የተለያዩ ግኝቶች በተለያዩ ጊዜያት ተገኝተዋል፡፡ የሉሲ(ድንቅነሽ) እ.ኤ.አ በ1974 ዓ.ም.፣ አርዲ እ.ኤ.አ 2009 ዓ.ም. እንዲሁም ሆሞሳፒያን ኢዳልቱ እ.ኤ.አ 1997 ዓ.ም. ከተገኙት ግኝቶቹ በዋናነት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ፋና ወጊነታችንን የሚያጠናክሩ ግኝቶች እየተገኙ ቢሆንም የመጀመሪያውን የሆሞ የቅድመ ሰው ዘር እድሜ ይታመንበት ከነበረው አመለካከት የቀየረና 2.8 ሚሊዩን ዓመት ያስቆጠረ ቅሪተ አካል ተገኝቷል፡፡ ይህ በአፋር ክልል በታችኛው አዋሽ ሸለቆ ሌዲ ገራሮ በሚባል የመካነ መቃብር ስፍራ የተገኘው ቅሪተ አካል የሰው ዘር የታችኛው ከፊል የመንጋጋ ክፍል ሲሆን በስነ-ህይወት ምድብ ጂነስ ሆሞ (Genus Homo) መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ 



2ኛው ሀገር አቀፍ የግእዝ ጉባኤ

በሀገራችን ከሚገኙ ጥንታዊ ቋንቋዎች አንዱ ግእዝ ነው፡፡ በርካታ ታሪኮች በዚሁ ቋንቋ ሰፍረው ይገኛሉ፡፡ በግእዝ የተጻፉ መዛግብትን መርምሮ ለመጠቀም ቋንቋውን ማወቅና መጠቀም የግድ ቢልም የግእዝ ቋንቋ ተናጋሪዎችም ሆኑ አንባቢዎች በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ብቻ የሚገኙ እየሆኑ መጥተዋል፡፡ የዘመናዊ ትምህርት መስፋፋት ግእዝን ከብዙሃኑ ህዝብ አራራቀው፡፡ አሁን ባለንበት ዘመን ደግሞ ለግእዝ ባይተዋር የሆነ በሚሊዮን የሚቆጠር አዲስ ትውልድ ተፈጠረ፡፡ ቋንቋው ከቋንቋነት ባለፈ በያዛቸው ፋይዳ ያላቸው እውቀቶች፣ ሀገራዊ እሴት በመሆኑና ብቸኛው የአፍሪካ የራሱ ፊደል ያለው ቋንቋ በመሆኑ ሊጠበቅ ብቻ ሳይሆን ሊለማም ይገባዋል፡፡ ሁለተኛው የግእዝ ጉባኤም ይህንኑ ዓላማ መሰረት አድርጎ ከመጋቢት 22 እስከ 23 ቀን 2007 ዓ.ም በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል፡፡



ምዕራብ አርሲ ዞን
አብያታ ሻላ ብሔራዊ ፓርክ
የምዕራብ አርሲ ዞን ከአዲስ አበባ በ250 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኝ የስምጥ ሸለቆ አካባቢ ነው፡፡ 12409.99 ስኩየር ኪሎ ሜትር የቆዳ ስፋት ያለው ይህ ዞን በሰሜን ምስራቅ ሸዋ ዞን፣ በደቡብ ጉጂ ዞን፣ በምዕራብ የደቡብ ብሔረሰብ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል እና በምስራቅ ባሌ ዞን ያዋስኑታል፡፡ አብዛኞቹ የዞኑ አካባቢዎች አማካኝ ከባህር ጠለል (ወለል) በላይ ከ1500 እስከ 3800 ሜትር ከፍታ አላቸው፤ የዞኑ ዋና ከተማ ሻሸመኔ ነው፡፡ ከዞኑ ኢንቨስትመንት ቢሮ ባገኘነው መረጃ መሰረት የዞኑ የህዝብ ቁጠር ከ2 ሚሊየን በላይ እንዲሚሆን ይገመታል፡፡

Thursday, April 23, 2015

አራተኛው ዓለም አቀፍ የቱሪዝም የንግድ ትርኢት አውደ ርዕይ
ዛሬ ተከፈተ፡፡

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት አዘጋጅነት የሚሰናዳውና ዘንድሮ ከሚያዝያ 15 እስከ 19/2007 ዓ.ም የሚቆየው አራተኛው ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ንግድ ትርኢት በኤግዚቢሽን ማዕከል ዛሬ ከሰዓት በኋላ በድምቀት ተከፍቷል፡፡

የንግድ ትርኢቱን አዲሱ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅትና 50ኛ ዓመት ኢዩቤልዩውን እያከበረ ያለው የኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ስራ ድርጅትን ጨምሮ በርካታ አስጎብኚ ድርጅቶች፣ የአዲስ አበባ አስጎብኚ ማህበር፣ የተለያዩ ሆቴሎች፣ የእደ-ጥበብ አምራቾች፣ የክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮዎች ተሳትፈውበታል፡፡ አውደ ርዕዩ ለቀጣዮቹ አምስት ቀናት ለጎብኚዎች ክፍት ሆኖ ይቆያል፡፡

Thursday, April 16, 2015



የቦንጋ ብሔራዊ ቡና ሙዚየም ተመረቀ፡፡
በሀገራችን የመጀመሪያው የሆነውና በደቡብ ክልል ካፋ ዞን ቦንጋ ከተማ የሚገኘው ብሔራዊ የቡና ሙዚየም ሚያዝያ 6 ቀን 2007 ዓ.ም ተመርቋል፡፡ ይህ በጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ የተመረቀው ብቸኛው የቡና ሙዚየም በሚሌኒየሙ መሰረተ ድንጋዩ የተጣለ ሲሆን ዓላማውም ካፋ የቡና መገኛ መሆኗን ለማረጋገጥ፤ በሀገሪቱ ከቡና ጋር ተያይዞ የሚገኙ እሴቶችንና የቡናን ብዝሃ ህይወት የተመለከቱ ስብስቦችን ለማኖርና ለትውልድ ለማሻገር ሲሆን ከቡና ጋር ተያይዞ ምርምርና ጥናት ለሚያደርጉም ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ሙዚየም ነው፡፡ ደረጃውን የጠበቀው ብሔራዊ የቡና ሙዚየም ከዚህ በኋላ ለጎብኚዎች ክፍት ነው፡፡



Wednesday, April 1, 2015



2ኛው የግዕዝ ጉባኤ በባህር ዳር ተካሄደ፡፡

በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቋንቋና ባህል እሴቶች ልማት ዳይሮክተሬት የተዘጋጀውና ከመጋቢት 22 ቀን እስከ መጋቢት 22 ቀን 2007 ዓ.ም ሁለት ቀናት የቆየው 2ኛው ሀገር አቀፍ የግእዝ ጉባኤ በስኬት ተጠናቀቀ፡፡ በባህር ዳር ከተማ የተካሄደው ይህ ጉባኤ በርካታ ምሁራን፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራማሪዎች፣ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት፣ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችን ጨምሮ ጉዳዮ የሚመለከታቸው አካላት ታድመውበታል፡፡
ጉባኤው በሁለት ቀናት ቆይታው ስምንት የሚደርሱ የውይይት መነሻ የጥናት ጽሑፎች ቀርበውታል፡፡ እነዚህም በቅድመ ክርስትና ተቀርጸው የተገኙ የድንጋይ ላይ ጽሑፎች ለኢትዮጵያና ለአካባቢው ያላቸው ታሪካዊ ፋይዳ፣ ጥንታዊ የብራና ጽሑፎች እንደ ሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ጽ/ቤት፣ የግዕዝ ሥነ-ጽሑፍ ጥቅም ለመካከለኛው ኢትዮጵያ ጥናት፣ ባህረ ሀሳብና ግዕዝ፣ የግዕዝ ቅኔና ፍልስፍናው፣ የግዕዝ ቋንቋ ትምህርት በአራቱ አድባራት ወ ገዳማት፣ ግዕዝና ሥነ-ጽሑፍ የሚሉ ርዕሶች ላይ ያተኮሩ የጥናት ጽሑፎች ናቸው፡፡
ዝግጅቱ ታሪካዊ የሆኑትንና በቅኔና አብነት ትምህርት ተቋምነታቸው የሚታወቁትን የምስራቅ ጎጃም ጥንታዊ አድባራትን የመጎብኘት መርሀ ግብርን አካቷል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የባህል ማእከልና ሌሎች አካላት የዝግጅቱ አጋሮች በመሆን ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡ አንደኛው የግዕዝ ጉባኤ አምና በተመሳሳይ ወቅት በአክሱም ከተማ መካሄዱ ይታወሳል፡፡