Monday, December 8, 2014


ነቀምቴ ከተማ

ነቀምቴ ከተማ የምስራቅ ወለጋ ዞን ርዕሰ ከተማ ስትሆን በስድስት ክፍለ ከተሞች የተከፋፈለች ናት፡፡ በከንቲባ ደረጃ በ1830 ዓ.ም አካባቢ በዘመኑ ገዥ በነበሩ በደጅ አዝማች ሞሮዳ በከሬ ጎዳና የተመሰረተችው ነቀምቴ ነቀምቴ የሚለውን ስያሜዋን ያገኘችው ቀደም ሲል በቦታው ላይ ይኖሩ ከነበሩ (ነቀምቴ ገዳአታ- መጫ) በሚባሉ ሰው ስም እንደሆነ ይነገራል፡፡ በወቅቱ በከፍተኛ ግምት የሚሰጠው የሲራራ ንግድ ከምፅዋ እስከ ማጂ-ከፋ ወርቅ፣ የባሪያ፣ የዝሆን ጥርስ፣ የጥርኝ የነብር ቆዳና የጨሌ ነጋዴዎች መመላለሻና መለዋወጫ ከዚያም የከብት የእህልና የተለያዩ ሸቀጦች መተላለፊያ ማእከል እንደነበረች ታሪክ ያወሳል፡፡ በ1937 ዓ.ም. በ18 ጋሻ መሬት ላይ የተቆረቆረችው ነቀምቴ በማዘጋጃ ቤት ደረጃ በከተማነት ተመዝግባ ህጋዊ እውቅና ያገኘችው ግን በ1942 ዓ.ም. ነው፡፡
ሶርጋ ሰው ሰራሽ ሀይቅ
 

ያሶ ወረዳ

በካማሺ ዞን ከሚገኙ አምስት ወረዳዎች መካከል አንዱ ሲሆን በ13 ቀበሌያት የተዋቀረ ነው፡፡ የወረዳው ቆዳ ስፋት 2858 ስኩዬር ካሬ ሜትር ሆኖ ከባህር ወለል በላይ ከ1200-2000 ሜትር ከፍታ አለው፡፡ መልካ ምድራዊ አቀማመጡም 50 በመቶ ሜዳማ፣ 30 በመቶ ተራራማ እና 20 በመቶ ሸለቆአማ ሲሆን የአየር ንብረቱ 91.8% ቆላማ እና 8.2%  ደግሞ ወይና ደጋ ነው፡፡ አማካይ የወረዳው የዝናብ መጠን ከ1200-1800 ሚሊ ሜትር ይጠጋል፡፡  የሙቀት መጠኑ በአማካይ 35ċ እንደሚሆንም ይገመታል፡፡ በ2005 ቆጠራ የወረዳው ህዝብ ብዛት ወንዶች 16082 ሴቶች 3581 ሲሆን በድምሩ 19663 ይሆናል፡፡ 
 

በወረዳው ታሪካዊና ተፈጥሮአዊ የመስህብ ሀብቶች ባለቤት ሲሆን ከነዚህም አያሙሳ ውሀ፣ ባጨጋንት ተራራ፣ ኮሚጳፍል ውሀ፣ የተፈጥሮ ዋሻ፣ ግሽሚላ ድንጋይ፣ ዳዱ ፏፏቴ፣ ፈወለወ ውሀና ቦንቅሽ ፓርክ ይገኙበታል፡፡

ማኦ ኮሞ

የማኦ ኮሞ ልዩ ወረዳ በቤኒሻምጉል ጉምዝ ክልላዊ መንግስት ደቡብ ምዕራባዊ ክፍል የሚገኝ ሲሆን ከአሶሳ በ115 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ የወረዳው ዋና ከተማ ቶንጎ ሲሆን የወረዳው አጠቃላይ የቆዳ ስፋት 210,000 ሄክታር እንደሚሆን ይገመታል፡፡ ልዩ ወረዳው በምዕራብ ከሱዳን፣ በሰሜን ከአሶሳ፣ በደቡብ ከጋምቤላ ክልል በምስራቅ ደግሞ ከኦሮምያ ክልል ጋር ይዋሰናል፡፡ በልዩ ወረዳው በዋናነት የማኦ፣ ኮሞ፣ በርታና ሌሎች ብሔረሰቦች የሚኖሩበት ሲሆን በ32 ቀበሌ የተዋቀረ ነው፡፡ የወረዳው ህዝብ ብዛት ከ63,000 በላይ እንደሚሆን የተለያዩ የሰነድ ማስረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በወረዳው የተለያዩ ባህላዊ ተፈጥሮአዊና ታሪካዊ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎች ይገኛሉ፡፡ ጥቂቶቹን በዚህ ዘገባ በጥቂቱ እንቃኛቸዋለን፡፡

ሸሞሎ ተራራ
 

መተከል ዞን

የመተከል ዞን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት ውስጥ ከሚገኙት ሶስት ዞኖች አንዱ ሲሆን በሰሜንና በምስራቅ ከአማራ ክልል፣ በደቡብ፣ በካማሽ /አባይ ወንዝ/ በምዕራብ ከሱዳን ጋር ይዋሰናል፡፡ በዞኑ በዋናነት የጉሙዝና የሽናሻ ብሄረሰቦች የሚኖሩ ሲሆን የኦሮሞ፣ የአማራ፣ የአገውና ሌሎች ብሄረሰቦች ማህበራዊ ትስስር በመፈጠር አብሯቸው ይኖራሉ፡፡ የዞኑ ዋና ከተማ ግልገል በለስ በቅርብ ጊዜ በ1993 ዓ.ም. የተቆረቆረች ከተማ ብትሆንም አካባቢዋ ለልማት ምቹ ከመሆኑ አኳያ የተፈጠረው ዕድገትና ለውጥ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡
 

የካማሺ ዞን

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከሚገኙት 3 ዞኖች መካከል አንዱ ነው፡፡ የዞኑ ዋና ከተማም ካማሽ ትባላለች፡፡ የክልሉ ርዕሰ ከተማ ከሆነችው አሶሳ በስተደቡብ ምስራቅ አቅጣጫ በ246 ኪሎ ሜትር ከአዲስ አበባ በስተምዕራብ አቅጣጫ ደግሞ በ512 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡
ጀሎ ተራራ ካማሽ ወረዳ ጀሎ ሌቃ ቀበሌ
 

የዞኑ ህዝብ ቁጥር 128,632 ሲሆን በአምስት ወረዳዎችና በ65 ቀበሌዎች የተደራጀ ነው፡፡ ዞኑን በደቡብ እና በምስራቅ ኦሮሚያ ክልል በሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ ከአሶሳና ከደቡብ ሱዳን እንዲሁም በሰሜን ከመተከል ዞንና ከአማራ ክልሎች ጋር ይዋሰናል፡፡ የአየር ንብረቱ ቆላማ ሲሆን በዞኑ በብዛት ሰፍሮ የሚገኘው የጉሙዝ ብሄረሰብ ነው፡፡