ሎካ አባያ
ከኢትዮጵያ ህዳሴ ጋር አብሮ የተበሰረው ፖርክ
ከሲዳማ ዞን ባህል ቱሪዝም መንግስት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ጋር በመተባበር
ሎክ አባያ በምሽት Locka abaya park |
በውቡና ለምለሙ የሲዳማ ዞን የሚገኘው ሎካ አባያ ፖርክ ለዞኑ የመጀመሪያው ነው፡፡ ከዚያ በአለፈ ከኢትዮጵያ የአዲስ ዘመን የእድገት ጉዞ ብስራት ጋር አብሮ መበሰሩ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን የወል የሆነ የደስታ ስሜትን ይፈጥራል፡፡ ሎካ አባያ ከሃዋሳ ከተማ ተነስተው ወደ ዲላ በሚወስደው መንገድ ተጉዘው አፖስቶ ሳይደርሱ በስተቀኝ ወደ ሎካ አባያ ወረዳ በመጓዝ የሚያገኙት ፖርክ ነው፡፡ ከፖርኩ በቅርበት የምትገኘዋ ከተማ ሐንጣጤ ትባላለች ከተማዋ ከሲዳማ ዞን ወረዳዎች አንዱ የሆነው የሎካ አባያ ወረዳ ዋና ከተማ ስትሆን ከሃዋሳ በ55 ኪ.ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ የሎካ አባያ ወረዳ 40.000 ሄክታር ስፋት ያለው ሲሆን የወረዳው ከፊል አካል በስምጥ ሸለቆ ክልል ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ ከአጠቃላዩ የቆዳ ሽፋን ውስጥ 83 በመቶ የሚሆነው ቆላማ (እርጥብና ደረቅ) የአየር ንብረት ያለው ነው፡፡ የወረዳው አማካኝ የሙቀት መጠን 20 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ይደርሳል፡፡
ጉዞአችን ወደ ሎካ አባያ ፖርክ ነው መንገዱ ለተሸከርካሪ ምቹ ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ ግራና ቀኝ የሲዳማ ብሄረሰብ የቆላ ቤት ውበትና የህብረተሰቡን አኗኗር እየተመለከቱ በማይሰለች ተፈጥሮ መሀል እየበረርን ነው፡፡ ግራና ቀኝ የሚያምርና አስገራሚ መልከአ ምድር እየተመለከትን የምንጓዝበት የሎካ አባያ ወረዳ ዙሪያ ገባ ሎካ አባያ ፖርክ ከመድረሳችን በፊት እራሱ በብዙ መልኩ በተፈጥሮ እንድንደመም የሚያደርግ ነው፡፡ ከሃገራችን ፖርኮች በእድሜው ወጣት ነገር ግን የሚያድግ ልጅ ከመሰረቱ ያስታውቃል እንዲሉ ከጀማሬው በርካታ ጥሩ ስራዎች የተሰሩበት ፖርክ ነው፡፡ የፖርኩ ባለሙያዎች ወጣቶች መሆናቸው ደግሞ እንደ ልብ በረው የሚሰሩ የነብር ጣቶችን የተሞላ ፖርክ ያደርገዋል፡፡
ወደ ፖርኩ የምናደርገው ጉዞ ቀላል ቀልጣፋና አስደሳች የመሆኑ ሚስጥር የፖርኩ ባለሙያዎች አብረውት ማደግ ለሚፈልጉት ፖርክና ለሥራቸው ያላቸውን ፍቅር የሚያሳይ ነው፡፡ አሁን የምንገኝበት ሥፍራ ከአዲስ አበባ በ340 ኪ.ሜትር ከሃዋሳ ከተማ ደግሞ70 ኪ.ሜትር ርቀት ላይ ነው፡፡ ለአዲስ አበባ ቅርብ ከሚባሉት ፖርኮች አንዱ ከሆነው የሎካ አባያ ፖርክ እንገኛለን፡፡ በቅርቡ በክልሉ አዲስ ከተከለሉ ፖርኮች አንዱ ሆኖ የተከለለው የሎካ አባያ ብሔራዊ ፖርክ ሰፊ ጥናት ተደርጐበት በሲዳማ ዞን ውስጥ በአባያ ሃይቅ ደቡባዊ አቅጣጫ ላይ የተዘረጋ ነው፡፡ 500 ኪ.ሜትር ስኩየር ቦታ የሚሸፍነውን የሎካ አባያ ፖርክ ለመከለል ህብረተሰቡን ያሳተፈ ሥራ መሰራቱን አቶ በዛብህ በየነ የሎካ አባያ ብሔራዊ ፖርክ አስተባባሪ ይገልፃሉ፡፡ እንደ አቶ በዛብህ ገለፃ ህብረተሰቡን በማወያየት ዘላቂ ጠቀሜታውን በማስረዳት በማካለሉ ሥራ አሳታፊ ሥራ ለመስራት ተችሏል፡፡ የፖርኩ ክፍል በሰሜን በኩል ከአባያ ሃይቅ፣ በደቡብ በኩልም እንደዚሁ የአባያ ሃይቅና የጉዶቦ ወንዝ በምዕራብ በኩል የብላቴ ወንዝ ያዋስኑታል፡፡ ሰፊው የፖርኩ ግዛት ከዚህ ቀደም በመኖሪያ መንደሮች የተሞላ አለመሆኑ ፖርኩን ከጅምሩ ጥብቅ ክልል የማድረጉ ሥራ የሰመረ ነው ለማለት ይቻላል፡፡
የፖርኩ ሌላኛ ውበት መልከአ ምድራዊ ገፅታው ነው፡፡ ከስምጥ ሸለቆው ገደል እስከ ተራራው መልኩ የፖርኩ አንድ ክፍል ነው፡፡ በስምጥ ሸለቆ ውስጥ ከሚገኙ ሃይቆች አንዱ የሆነውና ከሃገራችን ሃይቆች በስፋቱ የሁለተኛ ደረጃን የያዘው የአባያ ሃይቅ 1160 ስኩዌር ኪ.ሜትር የመሬት አካልን የሸፈነ ነው፡፡ አንዱ የአባያ ሃይቅ አካል በነጭ ሳር ብሔራዊ ፖርክ ክፍል ሲገኝ ሌላኛው የአባያ ክፍል በሎካ አባያ ብሔራዊ ፖርክ ይገኛል፡፡ 13 ሜትር አማካኝ ጥልቀት ያለው አባያ ሃይቅ ከ12 በላይ የተለያየ የአሳ ዝርያዎችን ጨምሮ በርካታ የውሃ ውስጥ እንስሳትን የያዘ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሎካ አባያ ብሔራዊ ፖርክ በውስጡ ከያዛቸው የተለያዩ አእዋፋትና እንደ አጋዘን፣ አንበሳ፣ አነርና የዱር ውሻን የመሳሰሉት የዱር እንስሳት ጋር ፖርኩ የውሃም የየብስም እንስሳት የሚገኙበት ፖርክ እንዲሆን አድርጐታል የሎካ አባያ ብሔራዊ ፖርክ እንዲሆን አድርጐታል የሎካ አባያ ብሔራዊ ፖርክ ለትራንስፖርት ምቹ መሆኑ ከሃዋሳ በቅርብ ርቀት ላይ መገኘቱና ፖርኩ በውስጡ የያዘው የመስህብ ሃብት የጐብኚዎችን ፍላጐት የሚያሟላ ሲሆን ሎካ አባያ ብሔራዊ ፖርክ ቱሪስቶች የውሃ ትራንስፖርትን በመጠቀም ከፖርኩ በቀጥታ ወደ አርባ ምንጭ ነጭ ሳር ብሔራዊ ፖርክ እና ጋሞ ጐፋ ዞን የማድረስ አቅም ያለው ነው፡፡ የሎካ አባያ ብሔራዊ ፖርክ ሥራ መጀመሩ ከመበሰሩ በፊት የፖርኩ ጽ/ቤት ግንባታ እና የባለሙያዎች ቅጥር የተከናወነ ሲሆን በቀጣይም የቱሪዝሙ ኢንድስትሪ በየግዜው የሚያሳየውን ፈጣን እድገት የተከተለ ልማት እንደሚከናወንለት ያላቸውን ተስፋ የፖርኩ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
ሎካ አባያ ብሔራዊ ፖርክ ሃገራችን የነደፈችውን ሁለንተናዊ የእድገት እቅድ በተለይም ብዝሃ ህይወትን ከመጠበቅ ተፈጥሮን ከመንከባከብና ከቱሪዝሙ ክፍለ ኢኮኖሚ ህብረተሰብን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሥራን ከመስራት አኳያ የፖርኩ እውን መሆን ለሃገራችንም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን ሰንቆ ብቅ ያለ እንዲሆን አድርጐታል፡፡ ሎካ አባያን የመጠበቅ የመንከባከብ የበለጠ የማልማትና የማስተዋወቁ ሥራ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ከሃገራችን ህዳሴ ጋር አብሮ የተበሰረው የሎካ አባያ ብሔራዊ ፖርክ የሃገራችን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ አንድ ጉልበት ሆኖ ብቅ ብሏል፡፡
ሎካ አባያ ብሔራዊ ፓርክን ይጐበኙ!!
No comments:
Post a Comment