ዜና
በጎንደር ከተማ ሁለት የአብነት ት/ቤቶች ተቃጠሉ

በእሳት ቃጠሎው የተማሪዎች ማደሪያዎች እና የመምህሩ መኖሪያ የነበሩ በአጠቃላይ ዘጠኝ ክፍሎች በውስጣቸው ከሚገኙ በ1714 ዓ.ም ከተጻፉ የብራና መጻሕፍተ መነኮሳት(ማር ይሥሓቅ፣ ፊልክስዩስ፣ አረጋዊ መንፈሳዊ) እና ሌሎች የኅትመት መጻሕፍት ጋራ ጨርሶ መቃጠላቸውን አስረድተዋል፡፡ እሳቱን ለማጥፋት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የእሳት አደጋ መከላከል መኪኖች እና የከተማው ምእመናን የተረባረቡ ቢሆንም ጉዳቱን ለመቆጣጠር የተቻለው ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዳይዛመት በማድረግ ብቻ ነበር፡፡
የመጻሕፍተ መነኮሳት ቤተ ጉባኤው በጠቅላይ ቤተ ክህነት እና በማኅበረ ቅዱሳን በጀት የተተከለላቸው በአጠቃላይ 15 መደበኛ ደቀ መዛሙርት እና ከከተማው አድባራት እየመጡ ትምህርቱን በግላቸው የሚከታተሉ በርካታ ተማሪዎች እንደነበሩት ደቀ መዛሙርቱ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ በሰጣቸው በታወቁት የአራቱ ጉባኤያት ሊቁ አየለ ዓለሙ በ1929 ዓ.ም የተመሠረተው ት/ቤቱ በአሁኑ ጊዜ ጉባኤው ማሄድ (መቀጠል) ያልቻለ ሲሆን መምህሩ ተሾመ ታደሰ እና ደቀ መዛሙርቱ በየምእመናኑ ቤት ተጠግተው እንደሚገኙ ተመልክቷል፡፡ ቤተ ጉባኤው የሚገኝበትና በ325 ዓ.ም ለአውግዞተ አርዮስ በኒቂያ በተሰበሰቡ 318ቱ ርቱዓነ አበው ሊቃውንት ስም የተሠራው - የሠለስቱ ምእት ቤተ ክርስቲያን በ1880 እና በ1881 ዓ.ም በወራሪው ድርቡሽ ጦር ለሁለት ተከታታይ ጊዜ ከተቃጠለ በኋላ ተመልሶ አልተሠራም፡፡
በተያያዘ ዜና በዚያው በጎንደር ከተማ የደብረ ብርሃን ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን የሚገኘውና በዐፄ አድያም ሰገድ ኢያሱ ዘመነ መንግሥት(17ኛው መ.ክ.ዘ) በኖሩት የቅኔ ሊቅ መምህር ክፍለ ዮሐንስ የተመሠረተው የገለአድ የቅኔ ቤተ ጉባኤ የካቲት ሁለት ቀን 2004 ዓ.ም በደረሰበት የእሳት ቃጠሎ ሙሉ በሙሉ መውደሙ ተገልጾአል፡፡
በዕለቱ ከቀትር በኋላ ከተማሪዎች ጎጆ የተቀሰቀሰው የእሳት ቃጠሎው መንሥኤ ለጊዜው ያልታወቀ ቢሆንም ተማሪዎች ወደ መኖሪያ ቤታቸው የገባውን ጉንዳን ለማራቅ የተጠቀሙበት እሳት እንደሆነ ተገምቷል፡፡ በቃጠሎው 26 የቅኔ ደቀ መዛሙርቱ መኖሪያዎች የሆኑ ጎጆ ቤቶች በውስጣቸው ከሚገኙ የተማሪዎቹ አልባሳት፣ መጻሕፍት እና ጥሬ ብሮች ጋር መውደማቸውን የዜናው ምንጮች ተናግረዋል፡፡
No comments:
Post a Comment