Thursday, January 26, 2012


ወገና - የሐድያ የሠርቶ መለወጥ ልዩ እሴት


ወገና ብዙ ነገር ነው የሥራ ፍቅር ሠርቶ ጥሮ ራስን የመለወጥ ባህል ነው፡፡ ከወገና ጀርባ በስኬት መከበርና መሞገስ አለ ወገና ጥበብ ነው፡፡
ብዙ ምስጢር ያለው ጥበብ ወገና በሐድያ ብሔረሰብ ባህል ከብቶችን መቶ ወይም ሺሕ በማለት ማስቆጠር ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ የጥረትን ውጤት በተዋበ ባህል ማስመረቅ ነው፡፡ ለወገና ሥርዓት የሚመረጠው ወቅት መስቀልን ከሚያስተናግደው ወርሃ መስከረም አንሥቶ እስከ ጥር ባለው ጊዜ ውስጥ ነው፡፡

ይህ ወቅት የጥጋብ ነው፡፡ መስኩ ለምለም የሚሆንበት ወራት በመሆኑ የሐድያ ከብቶች ሰውነት ይደልባል፤ በዚያ ላይ ወንዞች መጠናቸው ቀንሶ የጐርፍ ስጋት የማይኖርበት ነው፡፡ እነኚህ ሁሉ ተደምረው ወገና የሚከናወንበትን ወቅት ልዩ እንዲሆን አድርገጎታል፡፡ በወገና የከብቶች ቆጠራ ሥነ ሥርዓት ሁለት ደረጃዎች አሉ፡፡ የመጀመሪያው መቶ ከብቶችን የማስቆጠር ሥርዓቱ ጢቢማ ይባላል፡፡ ኩሚማ ደግሞ ሺሕ ከብቶችን የማስቆጠር ሥርዓት ነው፡፡

ማስቆጠር ማለት ማስመረቅንም የያዘ ነው፡፡ መቶ በማስቆጠሩ የጢቢማ ወግና ሥርዓት አንድ ሰው ከብቶቹ መቶ መሙላታቸውን ለማረጋገጥ አንድ ሁለት አስብሎ በማስቆጠር ማረጋገጥ ሲችል በሌላ መልኩ ደግሞ የቁልቋል ዛፍ ከበረት አዛባ መውጫ ላይ በመትከል ማስፈጸም ይችላል፡፡ ይህ የአቆጣጠር ባህል አንድን ሰው ይህን ያህል ከብት አለህ በሚል ብቻ ከብቶቹን ቆጥሮ ግለሰቡን የሚያሞካሽ ሳይሆን የከብቶቹን ምንጭ ለግለሰቡ ክብር እና ለሥርዓቱ እንደ ዋነኛ መስፈርት የሚቆጥር ነው፡፡ ይህም ከብቱን የሚያስቆጥረው ሰው ጥሮ ግሮ፣ ተፍጨርጭሮና ላቡን አንጠፍጥፎ አርብቶ መቶ ሲያደርስ ብቻ ነው፡፡ የሥራ ፍቅሩና ጥረቱ ከላቡ ውጤት ጋር ካልተደመረ ይሄንን ክብር ማግኘት አይቻልም፡፡ ያለ ስርቆትና ያለ ማጭበርበር በራሱ ጥረት ከብቶችን መቶ ማድረስ የቻለ ሰው ሐሜት ሳያገኘው ልጆቹ ሳያፍሩ እሱ ተከብሮ ይኖራል፡፡

ከዚህ ሥርዓት ጀርባ በሐድያ ባህል የጠበቀ ፉክክር አለ፡፡ አንዱ ከሌላው ላለማነስና ይሀንነ የወገና ክብር ለማግኘት ጠንክሮ ይሠራል፡፡ ወገናን አስመልክቶ በአቶ ኤርሲዶ አንተሴ ጥናታዊ ጽሑፍ ላይ ሥርዓቱ ሐድያ ከከብት እርባታ ከእርሻ ሥራ ጋር የጠበቀ ቁርኝት በነበረው የቀድሞ ጊዜ በሁሉም የሐድያ አካባቢዎች የሚከናወን መሆኑን ጠቅሰው አሁን አሁን ግን ሥርዓቱ በስፋት የሚካሔደው አርብቶ አደሩ ማኅበረሰብ በሚኖርበት ቆላማ አካባቢዎች እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ በወገና ሥርዓት ከገበያ የተገዛን ከብት ደምሮ ማስቆጠርን ባህሉ አያበረታታውም፡፡ ከዚህ ባለፈ የከብቶቹ መቶ ሞልቷል ሲባል የጥጆች ቁጥር ሳይጨመር ነው፡፡ ይህም ወግና ሥርዓቱን ለማከናወን የራሱ ሒደቶች አሉት፡፡ የግለሰቡና የሚስቱ ዘመዶች በተጠሩበት ይህንን ቁጥር የሚያፀድቁ ቡድኖች ይጋበዛሉ፡፡ እንደ ቅቤ፣ ማር፣ መጠጥና ምግብ ያሉት የእርድ ሰንጋዎች ይዘጋጃሉ፡፡ አዲስ በረት ለከብቶቹ ያዘጋጃል፡፡ ይህንን ሥርዓት ለመከታተል ለሚመጡ እንግዶች የሚሆን ማደሪያ ይዘጋጃል፡፡ እንደ አቶ ኤርሲዶ አንተሴ ጥናት ወገና ሁለት ምዕራፎች አሉት የመጀመሪያው ከቀኑ ዘጠኝ ሰዐት እስከ ሌሊቱ 11 ሰዓት ያለው ነው፡፡ ይህ ምዕራፍ ‹‹ቄቃስ›› ይባላል፡፡ በርካታ ተግባራት የሚከናወኑበት ነው፡፡

ሁለተኛው ቀን ሌሊት ጀምሮ ያለው ሥርዓት ደግሞ በድራንቻ የሐድያ ባህላዊ የሙገሳ ጨዋታ ጭፈራ የሚደምቅ ምዕራፍ ነው፡፡ በዚህ ሥርዓት በረቱ ተከፍቶ ከብቶቹ ሲወጡ መጀመሪያ የወጣውን ከብት የበኩር ልጅ፣ በመጨረሻ ላይ የወጣውን ደግሞ የመጨረሻ ልጅ ይወስዳሉ፡፡ በዚህ በወንዝ ማዶ በሚከናወን ሥርዓት በዚህ ሌሊት ማንም ሰው ከከብቶቹ ቀድሞ ወንዙን እንዲሻገር የሐድያ ባህል አይፈቅድም፡፡ ከብቶቹ የሚሻገሩበት ይህ ወንዝ ክረምት ከበጋ የማያቋርጥ መሆን አለበት፡፡ ይህ ደግሞ ሀብቱ የማያቋርጥ ለትውልድ የሚተላለፍ እንዲሆን ያላቸውን ምኞት የሚወክል ነው፡፡ ከብቶቹ ወንዝ ሲሻገሩ ይህንን ሥርዓት የሚያፀድቁት ኮሚቴዎች ትልልቅ ከብቶችን ይቆጥራሉ፡፡ ቁጥሩ ልክ ከሆነ ያ ሥፍራ የኮሚቴውን ማጽደቅ ተከትሎ በእልልታና በሆታ በጭፈራ ይደምቃል፡፡ ባልና ሚስት ቅቤ ይቀባሉ፤ የሹመት ሥነ ሥርዓት ይከናወናል፡፡ ከሹመቱ ስያሜዎች ብዙ ጊዜ የተለመደው አበጋዝ ነው፡፡ ይህ የጦር አበጋዝን ይወክላል፡፡ ከድህነት ጋር ታግለው ከፀሐይና ከዝናብ ጋር ተዋግተው በጥረት ባህላዊውን ክብር ተቀዳጅተዋል፡፡

በሐድያ ባህል ሥራና ጥረት ፍጻሜ የለውም፡፡ ለዚህ ነው በወገና ሥርዓት መቶ ያስቆጠረ ትጉህ፣ ሺሕ ሞልቶ ኩሚማ (ከብቶችን ሺሕ የማስቆጠር) ሥርዓትን ለማከናወን ይጥራል፡፡ ከብቶችን ሺሕ በማስቆጠር የወገና ሥርዓት እንደ መቶ ማስቆጠሩ ሁሉ የቆጠራ ሥርዓቱ ተመሳሳይ ሲሆን፣ በሺሕ የማስቆጠሩ ሒደት ከመቶ የሚለየው ሥርዓት ከብቶች ሜዳ ላይ አውጥቶ በእግራቸው ሥር ማዶ አሻግሮ በማየት ሰማይ ከታየ አልሞላም፤ ካልታየ ግን ሺሕ ሞልቷል የሚባልበት ሥርዓት ነው፡፡ ይህን ሺሕ የመሙላት ሥርዓት በድል ያጠናቀቀ ‹‹አዲላ ገራድ›› የሚል ማዕርግ ይሰጠዋል፡፡
ሐድያ በወገና ሥርዓት ሠርቶ መለወጥን በራስ ጥረት መከበርን በሥራ መግነንን የሚያሳይ ድንቅ እሴት ነው፡፡ (ቱባ፣ ሚያዝያ ፳፻፫)    

‹‹ዳጉ ባአህ››



‹‹ሰው በዜና ውሃ በደመና›› የሚል የኖረ ብሂል አለ፡፡ ሰው በዜና ይኖራል፡፡ ውሃም በደመና በኩል ይመጣል፡፡ ተረተኛው እንዲህ ያነፃፅረዋል፡፡
የዘመኑ ሳይንስና ቴክኖሎጂን ተከትሎ የመረጃ መለዋወጫ ደረጃው ከላቀ ደረጃ ከመድረሱና ዓለምን ወደ አንድ መንደር ከመለወጡ በፊት እንደየኅብረተሰቡ ወግና ልማድ፣ እንደየነገዱ አካሔድ የመረጃ መለዋወጫ ስልት ለዘመናት ኖሯል፡፡ አሁንም አለ፡፡ ከነዚህም መካከል አንዱ የአፋር የመረጃ ልውውጥ መንገድ ነው፡፡ በአፋርኛ ‹‹ዳጉ›› ይሰኛል፡፡

ሀገሬ ሚዲያ ባወጣው ‹‹ሀገራችንን እንወቅ - ቱባ›› ሕትመቱ ላይ ስለ ዳጉ ያብራራል፡፡ ዳጉ በበረሃማው ስነ ምህዳር የሚኖሩት አፋሮች አካባቢያቸውን ጠንቅቀው እንዲያውቁና የእርስ በእርስ ግንኙነታቸውን በዳበረ መረጃ ልውውጥ የታነፀ እንዲሆን ያስቻላቸው የባህል እሴት ነው፡፡ 


በአፋሮች ባህል ማዳመጥ ከመስማት በአለፈ ጠልቆ በመረዳት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ይኸ ደግሞ እንደ ዳጉ ባሉ የባህል እሴቶቻቸው ጎልቶ ይታያል፡፡ ዳጉ ማለት በአፋርኛ ወሬ፣ ነገር እንደማለት ነው፡፡ 

በዚህ ስልት እርስ በእርስ መረጃን ይለዋወጣሉ፡፡ በዚህ ስልት ተደማጭ ካልሆኑ ባለ ረጅም ሞገድ የሬዲዮ ስርጭቶች በፈጠነ ሁኔታ መረጃ ከአንዱ አካባቢ ወደ ሌላው ይደርሳል፡፡ ከመልካ ሰዲ ኤሊ ውሃ፣ ከበርሃሌ ዱብቲ፣ ከገዋኔ ኦፍዴራ በረሃማውን የአፋር ምድር ርቀት ሳይገድበው አብሮነታቸውን እንዲዳብር ያደረገው የአፋሮች እሴት ይህ ዳጉ የተባለ መረጃን የሚለዋወጡበት ስልት ነው፡፡ 

በአፋሮች ባህል ልብን ሰጥቶ ማዳመጥ የግድ ነው፡፡ ጫፍ ይዞ መሮጥም የለም ለዚህ ነው ባህላዊ የፍትህ ሥርዓታቸው ግጭትን በማስወገድ በኩል የተዋጣለት የሆነው፡፡ ነገርን ከመሠረቱ ያደምጣሉ ከመሰረተ ችግርን እንዲፈቱ ያግዛቸዋል፡፡ የዝናብና የግጦሽ ሁኔታ የግጭትን ዜና የአካባቢያቸውን ውሎ እየተቀባበሉ ይሰሙታል እናም እድሜ ለዳጉ አፋሮች አካባቢያቸውን በሚገባ እንዲያውቁ አድርጎአቸዋል፡፡ ያልነበሩበትን አካባቢ ወቅታዊ ሁኔታ በመረጃ ስልታቸው የነበሩ ያክል ያውቁታል፡፡ ዘመን የግንኙነትና የመረጃ ልውውጥ ጥበብን ሳያዳብር ዜናዎች በሳተላይት በረው ከየሰው ጆሮ መድረስ ሳይጀምሩ ኢትዮጵያ ዳጉን የመሰለ የመረጃ መለዋወጫ ስልት እሴት ባለቤት ነበረች፡፡ የዳጉ ስልት ግን በአማርኛ እንዳለው ትርጉም ቀለል ያለ ጉዳይ አይደለም፡፡ በእርግጥ አፋሮች እርስ በእርስ በሚኖራቸው ግንኙነት ወቅት ‹‹ዳጉ ባአህ›› ይባባላሉ፡፡ ይኸም መረጃ አቀብለኝ እንደማለት ነው፡፡ ጨዋታ አምጣ ብለን ልንወስደው እንችላለን፡፡ ይሁን እንጂ ጨዋታው ከፌዝነት ይልቅ መረጃነት ያለው መሆኑን የሚገልጽ ነው፡፡ 

በአፋሮች ባህል ሁለት አፋሮች እንደተገናኙ አንዱ ሌላኛው ይጠይቃል፤ ስለ ራሱ፣ ስለ ቤተሰቡ፣ ስለ መንደሩ፣ ስለ ጎሳውና ስሰማው ነገር ሁሉ ተጠያቂው ሁሉንም ይተርካል፤ ያደመጠው ደግሞ በተራው የራሱን ለሌላኛው ይነግረዋል፡፡ ዳጉ የተባለው ባህል ይህ ነው፡፡  

ቱባ፣ ስለ አፋር ክልል መስህቦቹም ያነሣል አፋሮች ባህልና ተፈጥሮ ህብር ሠርተው በተቀናጁበት ምድር የሚኖሩ ናቸው፡፡ ባህላቸው የፈጠረው ቀለም ምድራቸውን አስውበውታል፡፡ ምድራቸው በራሱ ተፈጥሮ የቸረችው ገጽታ ደግሞ ምትሃት ቢባል የሚቀል ድንቅ ውበት ነው፡፡ የኤርታ አሌ እሳተ ጎሞራ እስከ 1200 ዲሴ በሚደርስ የእሳት እቶን የሚንቀለቀል ስፍራ ነው፡፡ አፋሮች ኤርታ አሌ ያሉትም ለዚህ ነው፡፡ የሚጨስ ተራራ የሚል ትርጉም አለው፡፡

ከሦስት ሚሊዮን ዓመት በላይ ዕድሜን ያስቆጠረችው ሉሲም መገኛዋ በዚህ በአፋር ክልል ነው፡፡ ከሰመራ 136 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ሃዳር የተባለው ስፍራ በአፍሪካ ገናና ከሚባሉ የአርኪዮሎጂ ጥናት ቦታዎች አንዱ ለመሆን ችሏል፡፡ ከሉሲ ባሻገር እንደ ራሚደስ፣ ካዳባ፣ ጋርሂ ያሉ ቅሪተ አካሎች የተገኙበት የአፋር ክልል በፓርክ ሃብቱም ይታወቃል፡፡ የአዋሽ ብሔራዊ ፓርክ እና ገና ብዙ ያልተወራለት በአዘሎ ተራራ ሥር የተዘረጋው የያንጉዲራሳ ብሔራዊ ፓርክም መገኛ ነው፡፡ አሳአሌ ሐይቅ፣ አፍዴራና አቤ ሃይቆችና የዳሎል ረባዳ ምድር የአፋር ውብት ከሚገለፅባቸው መስህቦች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ እንደ ምድራቸው ተፈጥሮ ሁሉ በብዝሃ የባህል እሴቶች የሚታወቁት አፋሮች ዋንኛ የኑሮ መሠረታቸው የእንስሳት እርባታ ግብርና ነው፡፡ 

Monday, January 23, 2012


                   የጎንደር ከተማ አስተዳደር ህዝቡን በማሳተፍ ያሰራው እና 
                   ጥር 9/2004 ዓ.ም የተመረቀው የአጼ ቴዎድሮስ ሃውልት
ሐውልቱን ቀራጺ ብዙነህ ተስፋ የቀረጸው ሲሆን በፋይበር ግላስ የተሰራ ነው፡፡ ከአራት መቶ ሺ ብር የበለጠ ገንዘብ ፈጅቷል፡፡ በመሃል ጎንደር ፒያሳ ላይ የቆመው ይህ ሐውልት ከአጼ ቴዎድሮስ ባለ ሶስት ሜትር ሐውልት በተጨማሪ የልጃቸው የልኡል አለማየሁ እና የሴባስቶፖል መድፍ ምስሎች በልጥፍ ተቀርጸውበታል፡፡ ጎንደር ጥር 10 ቀን 2004 ዓ.ም ያሬድ ግርማ ባቋቋመው ድርጅት /ራእይ ለትውልድ/ አማካኝነት የታቀደውን የአቴ ቴዎድሮስ መታሰቢያ የትውልድ ማእከል ለማቋቋም በዞብል አካባቢ የመሰረተ ድንጋዩ ተጥሏል፡፡ ይህ ማእከል ቤተ-መጻህፍት፣ሙዝየምና የላቁ ተማሪዎች የሚማሩበት አዳሪ ት/ቤትን ያካትታል፡፡ የህንጻው ዲዛይን በአልቲሜት ፕላን/አርክቴክት በእግዚአብሄር አለበል/ ያለክፍያ የተሰራ ሲሆን ኪነ-ህንጻው ከጎንደር ቀደምት የኪነ--ህንጻ ጥበብ ጋር የተቀራረበ ነው፡፡ 


ጎንደር አይረሴ አስደናቂ የጥምቀት በዓል
የጎንደር ከተማ ወጣት የመንፈሳዊ ማኅበራት ጥምረት አባላት ውበት፣ኢትዮጵያዊነት እና ሃገር ተረካቢ ትውልድነት የተመሰከረበት በዓል
ከ100 ሺ ያላነሰ ጎብኚ ጎብኝቶታል፡፡
አቢሲኒያ የበረራ አገልግሎት ከሰማዩ ላይ እየቀዘፈ ከተራውና ጥምቀቱን አድምቆታል፡፡
የቦንጋ ከተማ ልኡክ በኢትዮጵያን በጎንደር ዝግጅት ላይ በመታደም ካፋ የቡና መገኛ ምድር መሆኑን አስተዋውቋል፡፡ ለጋኪ ሼሮቾ ምድር እንግዶች ጎንደር የአጼ ፋሲል ቤተ መንግስት ቅርጽን አበርክታላቸዋለች፡፡
በርካታ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት የታደሙበትን የዘንድሮን ኢትዮጵያን በጎንደር የአጼ ቴዎድሮስ ሐውልት ምርቃት አድምቆታል፡፡
ህይወት በአብያተ መንግስታት ግቢ በሚል የተዘጋጀው ትእይንት በአጼ ፋሲል ዘመን የቤተ-መንግስቱ ህይወት ምንይመስል እንደነበር የሚያሳይ ሲሆን በተመለከቱት ጎብኚዎች ዘንድ ከፍተኛ ስሜትን ፈጥሯል፡፡

Monday, January 16, 2012


ኢትዮጵያ በሰሜን ምስራቅ አፍሪካ 3-14 ዲግሪ ሰሜን እና 33-48 ዲግሪ ምሥራቅ የምትገኝ አገር ስትሆን የቆዳ ስፋቱዋም1,127,127 ካሬ .ነው። በሰሜን ከኤርትራ፣ በምዕራብ ከሱዳን፣ በደቡብ ከኬኒያ፣ እንዲሁም በምሥራቅ ከጅቡቲ እና ከሶማሊያጋር ትዋሰናለች። የኢትዮጵያ አብዛኛው ግዛት በተራሮችና በሀይቆች የተሞላ ሲሆን፣ ታላቁ የምሥራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ እነዚህኑከፍተኛ ቦታዎች ከሰሜን ምሥራቅ ወደ ደቡብ ምዕራብ በመጋደም ለሁለት ይከፍላቸዋል። በስምጥ ሸለቆው ዙሪያም በረሃማ የሆኑዝቅተኛ ቦታዎች ይገኛሉ። ይኅን መሰሉ የመልክዓ-ምድር ልዩነት አገሪቷ የተለያዩ የአየር ንብረት፣ የአፈር፣ የዕፅዋት እና የሕዝብአሰፋፈር ገጽታዎች እንዲኖራት አስችሏታል። በከፍታና በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ የተነሣ በኢትዮጵያ ውስጥ ሦስት ዐይነትየአየር-ንብረት ክልሎች ይገኛሉ። እነሱም:-
  • ደጋ - ከፍታቸው ከባሕር ጠለል 2400 ሜትር የሚጀምር እና የሙቀት መጠናቸው  16 ዲግረ . የማይበልጥ፤
  • ወይናደጋ - ከፍታቸው ከባሕር ጠለል 1500 እስከ 2400 ሜትር፣ ሙቀታቸውም 16 ዲግረ . እስከ 30 ዲግረ .የሚደርስና፣ 
  • ቆላ - ከባህር ጠለል በታች ጀምሮ እስከ 1500 ሜትር ከፍታ ያላቸው፣ የሙቀት መጠናቸውም 30 ዲግረ . እስከ 50ዲግረ . የሚደርስ አከባቢዎች ናቸው።
ዋናው የዝናብ ወቅት ከሰኔ አጋማሽ እስከ መስከረም አጋማሽ ሲሆን፣ ከሱ ቀደም ብሎ አልፎ አልፎ የሚጥል የበልግ ዝናብ በየካቲትእና በመጋቢት ይከሰታል። የተቀሩት ወራት በአብዛኛው ደረቅ ናቸው።


ኢትዮጵያ በሰሜን ምስራቅ የአፍሪካ ቀንድ በመባል በሚታወቀው አካባቢ የምትገኝ ከአፍሪካ በቆዳ ስፋቷ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ የምትገኘ አገር ናት፡፡ ዙሪያዋን አምስት አገሮች ያዋስኗታል፡፡ በምስራቅ በኩል ጅቡቲና ሶማሊያ፤ በሰሜንና በሰሜን ምስራቅ ኤርትራ፤ በደቡብ ኬንያ እና በምእራብ ሱዳን ናቸው፡፡ ጠቅላላ የቆዳ ሰፋት 1.1 ሚሊዬን ካሬ ሲሆን በውስጧ 7000 ኪ.ሜ የሚደርስ ርዝማኔ ያላቸው አስር ትላልቅ ወንዞችና ወደ 7000 ካሬ ጠቅላላ ስፋት ያላቸው ሀይቆች አሏት፡፡
መልክአ ምድር
ኢትዮጵያ በውስጧ የተለያዩ መልክአ ምድር ያላት አገር ከመሆኗ በተጨማሪ የአየር ንብረት አፈር የእንስሳትና የዕፅዋት ስብጥር የሚስተዋልባት አገር ናት፡፡ ኢትዮጵያ በጣም ከፍተኛ የሆኑ ተራሮች ከላያቸው ጠፍጣፋ የሆኑ አምባ የሚባሉ ኘላቶዎች ስምጥ የሆኑ ሸለቆዎች፤ ጥልቅ የወንዝ ሸለቆዎችና ሰፋፊ ሜዳዎች በውስጧ ይዛለች፡፡ ከባህር ጠለል በላይ 4620 ሜትር ከሚደርሰው ዳሽን ተራራ እስከ 148 ሜትር ከባህር ጠለል በታች እስከሆነው የዳሎል ዲኘረሽን ድረስ የሚሆን ልዩነት ያለው የከፍታና ዝቅታን የምታስተናግድ አገር ናት፡፡
ለም ከሆኑ መሬቶችና ተራሮች ምንም የማይታይባቸው ከሚመስሉ መሬቶች አንስቶ፣ ኢትዮጵያ በብዙ ገባሮችና ትላልቅ እንደ አባይ ተከዜ አዋሽ ኦሞ ዋቢ ሸበሌና ባሮ-አካቦ በመሳሰሉ ወንዞች የታደለች አገር ናት፡፡
ከሜዲትራንያን ምስራቃዊ መጨረሻ ተነስቶ፣ ደቡብ ምስራቅ አፍሪካ የምትገኘው ሞዛንቢክ ድረስ የሚደርሰው ታላቁ የስምጥ ሸለቆ ኢትዮጵያን ለሁለት ከፍሏት ያልፋል፡፡
የአየር ንብረት
ኢትዮጵያ እንደ መልክአ ምድራዊ አቀማመጧ የአየር ንብረቷም በተለያዩ ቦታዎች የተለያየ ሁኔታ ይታዩባታል፡፡ የመካከለኛው ኘላቶ አካባቢ ብዙም የማይፈራረቅ አይነት ወይናደጋማ አይነት የአየር ንብረት ይታይበታል፡፡ ዝቅተኛው የአየር ንብረት በአማካኝ 60c ሲሆን ነገር ግን ወደ ቀይባህር በረሀ አካባቢ 600c የሚደርስበት ጊዜዎች አሉ፡፡ በብዙ የአገሪቱ አካባቢ በክረምት ወራት ይኸውም ሰኔ ሀምሌና ነሀሴ ውስጥ ከፍተኛ የዝናብ መጠን ይመዘገባል፡፡ 
የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር
የኢትዮጵያ (እንዲሁም በኤርትራ አብያተ ክርስትያናት) ዋና ካሌንደር ነው። አዲስ ዓመት በጁሊያን ካሌንደር አቆጣጠር በኦገስት 29ወይም 30 የሚጀምር ሲሆን በግሪጎሪያን ካሌንደር ደግሞ ከ1901 እ.ኤ.አ. እስከ 2099 እ.ኤ.አ. ድረስ በሴፕቴምበር 11 ወይም 12ይጀምራል። በየአራት ዓመቱ አንድ ቀን ይጨመራል። በአንድ ዓመት ውስጥ አስራ-ሁለት ባለሠላሣ ቀናት እና አንድ ባለ አምስት(ስድስት በአራት ዓመት አንዴ) ቀናት ያሉባቸው ወራት አሉ።
የአመተ ምህረት ዘመናት ከጎርጎርዮስ 'አኖ ዶሚኒ' በ7 ወይም 8 አመታት የሚለይበት ምክንያት፣ ከኢየሱስ ክርስቶስ ልደት 400አመት ያህል በኋላ አኒያኖስ እስክንድራዊ ዘመኑን ሲቆጥረው ትስብዕቱ በመጋቢት 29 1 ዓ.ም. እንደ ሆነ ስለ ገመተ ይህበትስብዕት ዘመን 1ኛ አመት ሆኗል። ይህ አቆጣጠር በምሥራቅ ክርስቲያን አገራት ከተቀበለ በኋላም በ443 ዓ.ም. ከሮማ ፓፓናከምሥራቅ አቡናዎች መካከል ልዩነት ደርሶባቸው፤ በ517 ሌላ መነኩሴ ዲዮኒሲዮስ ኤክሲጉዎስ ሌላ አቆጣጠር (አኖ ዶሚኒ) አቀረበ።በሱ ግምት ትስብዕቱ የተከሠተበት ቀን ከአኒያኖስ ግምት በፊት በ8 አመታት አስቀደመው። አኖ ዶሚኒ አቆጣጠር በምዕራብአውሮፓ ላይኛነት በማግኘቱ የትስብእት ዘመን 1 አመተ ምህረት አኖ ዶሚኒ 9 እ.ኤ.አ ሆነ።
የኢትዮጵያ ዘመን ኣቆጣጠር የጁልያን ዘመን ኣቆጣጠር ኣይደለም።
ወራት
የወራት አቆጣጠር የተወረሰ ከቅብጢ ዘመን አቆጣጠር፣ ይህም የወጣ ከጥንታዊ ግብጽ ዘመን አቆጣጠር ነው። ሆኖም የወሮችስሞች በግዕዝ ተለውጠዋል።
አማርኛ
ጎርጎርዮስ
በሰግር ዓመት
መስከረም
ሴፕቴምበር 11
ሴፕቴምበር 12
ጥቅምት
ኦክቶበር 11
ኦክቶበር 12
ኅዳር
ኖቨምበር 10
ኖቨምበር 11
ታኅሣሥ
ዲሴምበር 10
ዲሴምበር 11
ጥር
ጃንዋሪ 9
ጃንዋሪ 10
የካቲት
ፌብርዋሪ 8
ፌብርዋሪ 9
መጋቢት
ማርች 10
ማርች 10
ሚያዝያ
ኤፕሪል 9
ኤፕሪል 9
ግንቦት
ሜይ 9
ሜይ 9
ሰኔ
ጁን 8
ጁን 8
ሐምሌ
ጁላይ 8
ጁላይ 8
ነሐሴ
ኦገስት 7
ኦገስት 7
ጳጉሜን
ሴፕቴምበር 6
ሴፕቴምበር 6