Friday, June 12, 2015



       ለ3ኛ ጊዜ የተዘጋው ሆቴል ሾው ኢትዮጵያ 2007 የሆስፒታሊቲና ቱሪዝም ፎረም እና ኤክስፖ ተከፈተ፡፡
ሜሮን ታምሩ

ከሰኔ 4-7 2007 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ የሚካሄደው የሆቴል ሾው ዓለም አቀፍ ደረጃ የያዘ፣ በአፍሪካ አህጉር ታዋቂነትን ያተረፈ በኢትዮጵያ መሰረት ላይ የተገነባ የሆስፒታሊቲና የቱሪዝም መድረክ የመፍጠርና ለሀገራችን የሆቴልና ቱሪዝም ኢንዱስትሪ ባለድርሻ አካላት ጋር መድረክ በማዘጋጀት በዓለም አቀፍ ደረጃና በሀገር ውስጥ የሚታዩ የኢንዱስትሪ ነክ ጉዳዮች ለመዳሰስ እና አዳዲስ የአሰራር ዘዴዎችን ለማካፈል እንዲሁም የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡




በዚህ የሆስፒታሊቲና ቱሪዝም ምርትና አገልግሎት ኤክስፖ 145 ዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ ድርጅቶችና ተቋማት የተሳተፉ ሲሆን በተጨማሪም ተሳታፊ ድርጅቶች በጋራ ከ250 በላይ አለም አቀፍ መልካም ስም ያላቸው የሆቴል/ የሆስፒታሊቲ/ አገልግሎት መስጫ መሳሪያዎች እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የንግድ መለያዎች ይወክላሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ኤክስፖው ከቀላል እስከ ከፍተኛ መገልገያ መሳሪያዎችና እና ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የሚቀርቡበት መድረክ ሊሆን ችሏል፡፡
በአራት ተከታታይ ቀናት ቆይታውም ሁለት ከፍተኛ ደረጃ ያላቸው የውይይት መድረኮች፣ የተለያዩ ሙያዊ ውድድሮች፣ ትውውቅና የንግድ ትስስር የመፍጠሪያ ተግባራት ይከናወናሉ፡፡
በመክፈቻው ላይ የተገኙት የመንግስት ኮሚኒኬሽን ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን ይህ ኤክስፖ ለአገራችን መልካም ገፅታ ግንባታ ትልቅ አስተዋፅኦ ሲኖረው በሆቴልና በቱሪዝም ዘርፉ ባለሆቴሎችን ጥራት ካላቸው እቃ አቅራቢዎች ጋር የሚያገናኝና ዘርፉ ማደጉን ተከትሎ አቅራቢዎችም በአገራችን ላይ ጥራት ያላቸው እቃዎች አምርተው ከፍተኛ ተጠቃሚ የሚሆኑበት መንገድ ይፈጥራል፡፡ መገለጫችን ጥራት ሲሆን ፍላጎት ጥራትን ይወልዳል፤ ጥራት ያለው አቅርቦት ሲኖር ተጨማሪ ፍላጎቶችን ስለሚወልድ በቀጣይ በዘርፉ ከፍተኛ የሆነ ለውጥ እና እድገት ይመጣል ብለዋል፡፡

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ አሚን አብዱቃድር የቱሪዝምና የሆቴል ኢንዱስትሪው በህብረተሰቡ ዘንድ ትልቅ ግንዛቤ የፈጠረና ለኢኮኖሚያችን፣ ለስራ እድል ፈጠራ፣ ለመልካም ገፅታችን ወሳኝ እንደሆነ እየተረዳን ነው፡፡ የግል ሴክተሩም የራሱን ድርሻ እየተወጣ ትልልቅ ስራዎች እየተሰሩ ነው፡፡ እንደ መንግስትም እንደዚህ አይነት የንግድ ትርኢቶችን እናበረታታለን፤ በቀጣም ሌሎች ኢግዚቢሽኖች አገራችን ላይ እንዲከናወኑ ትልቅ ልምድ እና በራስ የመተማመን አቅም ፈጥሮልናል ብለን ነው የምናስበው፡፡ በዋናነትም ሆቴሎቻችን ለመልካም ገፅታ ግንባታ ትልቅ ሚና ስለሚጫወቱ አለም አቀፍ አውቅና ያላቸው መሆን አለባቸው፡፡ የኤክስፖ አቅራቢዎችና አማካሪዎች የበለጠ ከኢትዮጵያ አቻዎቻቸው ጋር የሚወያዩበት የሚመካከሩበት በቀጣይም በሆቴልና በቱሪዝም በሌሎች ዘርፎች ላይ በጋራ የሚሰሩበትና ሆቴሎቻችን በእጅጉ ለጎብኚዎች ለተጠቃሚዎች ለሌላው ህብረተሰብ ምቹ ለማድረግ የሚሰራበት ሂደት ነው ያለው፡፡ ሆቴሎቻን አቅርቦትና ጥራት የአገራችንን የኢኮኖሚ ደረጃ ማሳየት ይኖርባቸዋል፡፡ ለዚህም ይህ ኤክስፖ ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡ በማለት ገልፀዋል፡፡
ከሆስፒታሊቲና ቱሪዝም ምርትና አገልግሎት ኤክስፖ በተጨማሪ በመጋቢት ወር 2008 ዓ.ም የሚካሄደው የማይስ- ምስራቅ አፍሪካ 2008 ፎረም እና ኤክስፖ በኢትዮጵያ እንዲካሄድ ውሳኔ በመደረሱ የምስረታ ፕሮግራም ተከናውኗል፡፡

No comments:

Post a Comment