የግዮን ላይ ለዛ
Blue Nile |
ግዮን ያለ ሀሳብ ይወርዳል፡፡ የዘፍጥረት መጽሐፍ ኢትዮጵያን ይከባል ቢለውም በአራት ወገን ከተከፈሉት አራት ወንዞች
አንዱና ኤደን ገነትን የሚያጠጣ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ አባይ አባይ ብለን የተቃኘንለት ግዙፍ ወንዝ የ1440 ኪሎ ሜትር ጉዞውን
ከሚጀምርበት በራፍ….ግዮንን ተማምኖ ኑሮውን የሚኖር ሰው ነው፡፡ ህብርሰው ምህረት ይባላል፡፡ አስራ ሁለት ዓመታት እንዳለፉት የሚናገረው
ህብር ሰው ሰዎችን ከጢስ አባይ ከተማ ዳርቻ ወደ ጢስ አባይ ፏፏቴ ያሻግራል፡፡
ብሉበርድ የህብር ሰው ሞተር ጀልባ ናት፡፡ ከሞተር ጀልባዋ ላይ ሆነን ወደ ማዶ ልንሻገር እምነታችንን ሁለቱ ላይ
ጣልን….ጀልባዋና ባለቤቷ ህብርሰው ላይ….እናም በሚሔደው አባይ ገላ ላይ ወደ ጎን ሔድንበት….
እንዴት ነው የሀገር ውስጥ ቱሪስት ቁጥር ምን ይመስላል? አልንው ወጣቱን "የሀገር ውስጥ ወቅታዊ እና የተወሰነ ነው በክረምት ላይ በግሩፕ
ይመጣሉ ባጠቃላይ ጥሩ እንቅስቃሴ ነው ያለው፡፡" ጉዞአችንን እንደቀጥልን ነው አባይ ማለት ለእኔና ለቤተሰቦቼ የሚለው ህብርሰው
ከዚህ ታላቅ ወንዝ አንዳች የህይወት ትስስር እንዳለው ተረከልኝ፡፡ በርካታ ቱሪስቶች ወደዚህ ስፍራ እንደሚመጡ የሚናገረው ህብርሰው
ስፍራውን እንዲጎበኙ በማድረግ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ ይናገራል፡፡
ማዶ እንደተነሳን የደረሱ ተሻጋሪዎች መመለሳችንን ይጠብቃሉ….. ህብር ሰው አካባቢውን እየተመለከተ ገለጻውን ቀጥሏል በተለይ ገጠመኞቹን "እዚህ እኛ አካባቢ ላይ በእርግጥ አዞ አለ፤
ግን ለማዳ ነው፤ እስካሁን ሰው ተተናኩሎ አያውቅም ቱሪስቶችም ማየት ሲፈልጉ ባሉበት ቦታ ወስደን እናሳያቸዋለን እስካሁን አደጋ
ደርሶ አያውቅም፡፡"
ዋናስ ላይ እንዴት ነህ?
"ዋና እችላለሁ እዚህ አካባቢ ህፃናት ሳይቀሩ ዋና ይችላሉ፡፡"
አባይ እንደሞላ ነው….ጥለቁብኝ ጥለቁብኝ ይላል….ደግሞ መልሶ ያስፈራል፡፡ ህብርሰው እንደዚህ ያለ አጋጣሚ እንዳለው
ነገረን "አንዳንዴ ውሃ ሲሞላ ቱሪስቶች ለማየት ካላቸው ጉጉት የተነሳ ውሃው በጣም ሞልቶ ወደዛ መቅረብ አለብን የሚል ጥያቄ
ያነሳሉ እኛ ግን አስቸጋሪ በመሆኑ ብዙ ጊዜ ፍቃደኛ አንሆንም አንዳንዴ እየሄድክ እንደአጋጣሚ ሞተር ይጠፋብሀል እንግዳ የሆነ ሰው
ይደነግጣል ግን ምንም ችግር የለውም፡፡ ያለሞተር መሄድ ይቻላል ለጥንቃቄ በሚል እንጂ ያን ያህል የሚያስቸግር ነገር የለም፡፡"
እንዲህ ያለው ቦታ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ሊመለከቱት የሚገባ ብዙ ወጪ የማያስወጣ በህይወት ዘመን ግን ሊረሳ
የማይችል ትዝታን የሚያተርፉበት ስፍራ ነው፡፡ የጎብኚውን ነገር አነሳንለት….ሳይመልሰው መውረጃችን ደረሰ…..ምላሹን ስንመለስ አልንው….ፈገግታ
አልተለየውም፤
ከጢስ አባይ መልስ…..ብሉበርድ ጀልባና ቀዛፊዋ ህብርሰው
"ቆንጆ ነበር?"…አለን ገና ስንደርስ….ደስታችንን ከፊታችን አነበበው ቀጠለ "አንደኛ
የቱሪስትመዳረሻ ቦታዎች ነፃ መሆን መቻል አለባቸው፡፡ ከመንገድ ችግር እንዲሁም በቱሪስት ማረፊያዎች ለምሳሌ እዚህ ጭስ አባይ ፏፏቴው
አካባቢ ላይ ምንም አይነት የተዘጋጀ ሎጅ የለም ምን አልባት ከባህርዳር ቅርበት የተነሳ እንደሆነ አላውቅም በተለያየ ጊዜ ይሰራል
እየተባለ እስካሁን ሊሰራ አልቻለም፡፡ ብዙ ጊዜ ቱሪስቶች እዚህ አካባቢ ለምን ማረፊያ አይዘጋጅም የሚል ጥያቄ ያነሳሉ ከእዛ ውጪ
በዚህ አካባቢ ላይ ለቱሪስቶች የሚያስቸግር ነገር የለም ግን የበለጠ መዳረሻ ቢኖር ቱሪስቱ እያደረና እረፍት የእያደረገ ቢጎበኝ
ጥሩ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ላይ ብዙ ነገሮች ቢሰሩ የአካባቢው ሰው ተጠቃሚ የሚሆንበት ነገር ይኖራል፡፡"
እኛ ስንመለስ ገና ወደ ጢስ አባይ ለመሄድ የተዘጋጀው ጎብኚ ብዙ ነበር….ገበያው የደራለት ህብርሰው ቆሞ የሚጠብቀውን
መንገደኛ ተመለከተና "የዛሬው ጎብኚ ጥሩ ነው በእርግጥ አንዳንዴ የሚበዙበት አጋጣሚ አለ ዛሬ ግን በተወሰነ ደረጃ ጥሩ
ነው፡፡ " አለን
13 ጀልባ ባለበት የአባይ ወንዝ ግፋ ቢል በወር አንድና ሁለት ጊዜ ተራ ይደርሳቸዋል፡፡ ያም ቀን ተጓዥ የሌለበት
ሊሆን ይችላል፡፡ እንደዛሬው የገድ ቀን ከሆነ ደግሞ ከ300 እስከ 400 መንገደኛ ያመላልሳሉ፡፡
አካባቢውን በተመለከተ ትልቅ ችግር አለ የሚለው ህብርሰው ስለስፍራው "በየጊዜው ስላው ችግር ይነገራል ግን ማንም ያንን ጥያቄ ሲፈታ አናይም
እንዳያችሁት የመንገድ ችግር አለ፤ በተጨማሪም ለእንግዶች የሚሆን ማረፊያ የለም፡፡ በእንደዚህ አይነት የቱሪስት መስህብ ቦታ ላይ
እንደዚህ አይነት ችግሮች ቢቀረፉ የተሻለ ነው፡፡ አሁን እናንተ እንደ አጋጣሚ ሆኖ በደረቅ ሰዓት ላይ መጥታችሁ እንጂ ብዙ ቱሪስቶች
በመንገድ ላይ የሚጉላሉበት ጊዜ አለ፡፡ ይህ 25 ኪ.ሜ አስፓልት ቢሆንም ለቱሪዝምና ለመብራት ሀይል ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡ ብዙ
ጊዜ ይታሰብበታል፣ በርካታ ጊዜ ችግሮችን እናነሳለን ግን ምላሽ የለም፡፡" ወደ መዳረሻችን እየቀረብን ነው…ህብር ሰውና
አባይን ጥለን ልንወረድ ጥቂት ቀርቶናል፤ ህብርሰው ለአባይ ወንዝ ያለው ፍቅር ከአይነውሃው ይነበባል ደግሞም ይገልጸዋል፤
"አባይ ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለአካባቢው ህብረተሰብ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው፡፡ አንደኛ እኔ ቤተሰቤን የማስተዳደረው
በእዚህ ስራ ነው አሁን በምታያት ብሉበርድ ጀልባ ከ12 ዓመት በላይ ሰርቼባታለሁ፡፡ በዚህ ቱሪስት ሲያልፍ ከቱሪስቱ በተጨማሪም
ደግሞ የዚህ አካባቢ ህብረተሰብ በዚህ ሲያቋርጥ በተለያየ መልኩ በማሻገር የቤተሰቦቻችንን ህይወት የምንመራበት የገቢ ማግኛ ምንጭ
ነው፡፡ በእርግጥ አባይ የማያልቅ ሀብት ነው፡፡ በዚህ በማያልቅ ሀብት ላይ በርካታ ነገሮችን መስራት ይቻላል፡፡ ሆቴሎች ቢስፋፉ
መንገዱ ቢስተካከል ከባህርዳር ባልተናነሰ ሁኔታ ቱሪስቱ እዚህ እየቆየ ይሄዳል፡፡ እነዚህ ነገሮች ቢስተካከሉ የተሻለ ስራ መስራት
ይቻላል፡፡ እንዲሁም የአካባቢው ህብረተሰብ ተጠቃሚ ይሆናል በተጨማሪም መንግስት ከቱሪዝም የሚያገኘው
ገቢ እያደገ ይሄዳል ብዬ አስባለሁ፡፡"
ጋዜጠኞች መሆናችንን አወቀ…..ከብሉበርድ ጀልባ ላይ ስንወርድ "እንግዲህ እስካሁን ላልጎበኙት ሰዎች ጥሩ
መስህብ ያለበት ቦታ ስለሆነ መጥተው ይጎብኙት ነው የምለው፡፡" አለን…እነሆ ማድረስ አይደለ ስራችን…..
No comments:
Post a Comment