Monday, May 7, 2012


የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ሰራተኞች

የሃገርህን እወቅ ክበብ የሶስት ቀናት ጉዞ

እውቀት ከራስ ይጀምራል፣


ባህልና ቱሪዝም
ልኡኩ ሲንቀሳቀስ
የሃገር ውስጥ ቱሪዝም እንደቱሪዝም ኢንዱስትሪ ዘርፍነት ብቻ የሚታይ አይደደለም፣ ጠቀሜታዎቹ በርካታ ናቸው፣ በተለይም ዜጎች ለሃገራቸው ቅርስ፣ባህልና እሴት መጠበቅ መልማትና መተዋወቅ የዜግነት ድርሻቸውን እንዲወጡ ለማድረግ ቁልፉ መንገድ የሃገር ውስጥ ቱሪዝምን ማስፋፋት ነው፡፡

ወደ ራሱ ጓዳ ብዙም ሳይሳካለት የኖረው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር መስሪያ ቤት፣ በተቃራኒው ለሃገር ውስጥ ቱሪዝም መስፋፋት ሲያደርግ በነበረው ጥረት በርካታ መስሪያ ቤቶች ቢያንስ በአመት አንድ ግዜ ጉብኝት እንዲያደርጉ ያስቻሉ የሃገርህን እወቅ ክበባት እንዲቋቋሙ አድርጓል፡፡ ይህም ሆኖ ብዙዎች ላይ ጥያቄ የፈጠረው የራሱ የሚኒስቴር መስሪያቤቱ ሰራተኞች የሃገርህን እወቅ ክበብ መቼ ይሆን ሃገሩን ለማወቅ እግሩን የሚያነሳው የሚለው ነበር፡፡


ቅዳሜ መጋቢት 27 ቀን 2004 ዓ.ም የሚኒስቴር መስሪያቤቱ ሰራተኞች የሃገርህን እወቅ ክበብ የመጀመሪያው የጉብኝት ጉዞ የመጀመሪያው ቀን ነበር፣ የጉዞው ቅንጅት ከጅማሬው ያምር ስለነበረ ይህን ክህሎት ይዘው እስከ ዛሬስ ስለምን የጋን ውስጥ መብራት ሆኖ አስብሎናል፡፡
የጉዞ ምእራፍ

ከሚኒስቴር መስሪያቤቱ ቅጥር ግቢ የተነቃነቀው ተጓዥ ከ120 በላይ ሲሆን መልካም ጉዞ ሲሉ ክብርት ወ/ሮ ታደለች ዳለቾ ጉዞውን አስጀምረዋል፡፡ የመልካ ቁንጥሬ መካነ ቅርስ እስከ ሙዚየሙ፣የአዳዲ ማርያም ቤተ-ክርስቲያን እና የጢያ ትክል ድንጋይ የመጀመሪያ ቀን የተጎበኙ ስፍራዎች ነበሩ፡፡
ቡታ ጅራ ከዘቢደር ተራራ ግርጌ አርፈን፣ምርጥ የጉራጌ ክትፎአችንን ካጣጣምን በኃላ ጉዞአችንን ቀጠልን፣ ወደ ሃዋሳ ሃዋሳ የሚገኘው የሃይሌ ሪዞርትም በወፍ በረር ከተጎበኙ ስፍራዎች አንዱ ነው፣ ምሽቱን ስለ ቀኑ እያወራን ያማረ ሆቴል እራትን ከካንፋየር ጋር በመዝናኛ አጅበን አስተናገድንው፣

ይህ ጉዞ ከሌሎች መስሪያ ቤቶች ጉዞ የሚለይበት በርካታ መልክ አለው፣ ይህ ተቋም እራይ ሰንቋል፤ በ2012 የሃገሪቱ ባህላዊ እና የተፈጥሮ መስህብ ሃብቶች ለምተው በአህጉራችን በቱሪዝም መዳረሻነት ከሚመረጡ አምስት ግንባር ቀደም ሃገሮች አንዷ እንድትሆን ያልማል፤ ተቋም ይህን የሚያልመው መላ የሰው ኃይሉን ተማምኖ ነው ባለእራዩም ሰው ነው፣ ራዕዩን የሚያሳካውም ሰው ነው፡፡ ለአንድ ተቋም ራዕይ ስኬት ትልቅ ትንሽ የሚባል ሰራተኛ የለም፣ ሁሉም ለራዕዩ ስኬት የሚሰራ ድር ነው፡፡ ለዚህም ነው ከሁሉም ስራ ዘርፍ የተውጣጡ ሰራተኞች ያቋቋሙት የሚኒስቴር መስሪያቤቱ ሰራተኞች የሃገርህን እወቅ ክበብ የመጀመሪያ ጉዞ መዝናኛ ብቻ ሳይሆን ራዕይን ለመገንዘብ የሚደረግ ሃሰሳ የሚሆነው፣

በእኛ እምነት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሰነቀው ራዕይ እንዲሳካ ራዕዩን የሚያስፈጽመው አካል ስለራዕዩ በእጅጉ ሊረዳ ይገባል፡፡ ይህ ጉዞ የመስክ ጉብኝትም የመስክ ስራ ምልከታም ልንለው እንችላለን በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ… ይህንን በመረዳትም ይመስለናል ክብርት ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ታደለች እንደ ማኅበሩ አባልም እንደ ስራ ኃላፊም አብረው የተጓዙት፡፡

ሌላው የጉዞ ጣዕም በአካባቢ ጥበቃ ላይ አባላቱ ያደረጉት ተግባር ነው፡፡ ቱሪዝም ለወንድማማችነት ያለውን ሚና ያሳየው የታቦር ተራራ የችግኝ ተከላ ሥነ-ሥረዓት የጉዞው አንድ አካል ነው፣ አባላቱ በሃዋሳ ቆይታቸው ለፍቅር ሃይቁ ውበት ዋስትና የታቦር ገላ በእጽዋት መሸፈን አለበት፣ የሚኒስቴር መስሪያቤቱ ሰራተኞች የሃገርህን እወቅ ክበብ አባላት በታቦር ተራራ ያሳረፍት ይህንን ህያው ማስታወሻ ነበር፡፡

 እስከ ሰኞ በቆየው የሶስት ቀናት ጉብኝት ወንዶ ገነትና ሶደሬን ጨምሮ የቆቃ ኃይል ማመንጫ ተጎብኝተዋል፡፡ የሃገርህን እወቅ ክበባት ሰራተኛን በማነቃቃት/የመዝናኛ ስሜትን በመፍጠር/ በሰራተኛው መካከል ቤተሰባዊ ግንኙነትን በማዳበርና ሀገርን በማወቅ በኩል የሚኖራቸው ሚና በእርግጥም ትክክል መሆኑን ያስመሰከረው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ሰራተኞች የሃገርህን እወቅ ክበብ የጉብኝት ጉዞ ቅዳሜ ሚያዝያ 27 ቀን 2004 ዓ.ም ከጠዋቱ 12፡00 ተጀምሮ ሰኞ ሚያዝያ 29 ቀን 2004 ዓ.ም ከምሽቱ 12፡00 ተጠናቀቀ፡፡   

No comments:

Post a Comment