Wednesday, April 18, 2012

ቱባ ሚያዝያ እትም
ቱባ መጽሄት






ኮንሶ
የኮንሶ ወረዳ በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች ህዝቦች ክልላዊ መንግስት በአዲሲቷ ሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን ሥር ከሚገኙ አምስት ወረዳዎች አንዷ ስትሆን ከአዲስ አበባ በ595 ኪ.ሜትር ርቀት ላይ ከሀዋሳ ደግሞ በ365 ኪ.ሜትር ርቀት ላይ በደቡባዊ ምስራቅ ወደ ደቡብ ኦሞ  ጅንካ ከተማና እንዲሁም ወደ ያቤሎና ሞያሌ መስመሮች በሚወስዱ መንገዶች መስመር ላይ ትገኛለች፡፡
በ41 የገጠር ቀበሌያትና በሁለት ከተማ አስተዳድሮች የተዋቀረው የኮንሶ ወረዳ የኮንሶ ብሔረሰብ መኖሪያ ነው፡፡ በወረዳው ከ897 ሺ በላይ ህዝብ ይኖራል፡፡ የኩሽ ቤተሰብ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑት ኮንሶዎች በሚኖሩበት ምድር ከ500 ዓመታት በላይ እድሜ ያላቸው የብዙ ተመራማሪዎችን ትኩረት ለዓመታት ስበው የኖሩ ቅርሶች ለትውልድ መተው የቻሉ ህዝቦች ናቸው፡፡
ኮንሶ ከባህር ጠለል በላይ ከ500-2010 ሜትር ከፍታ ባለው ስፍራ ሲገኝ በሰሜን ከደራሼ፣ከቡርጂ አማሮ፣ በስተምዕራብ ከደቡብ ኦሞ ዞን፣ በደቡብ ደግሞ የኦሮምያ ክልል ያዋስኑታል፡፡ ኮንሶ በእጅጉ የታወቀ ለበርካታ ዓመታት የሥነ-ሰውና ሥነ-ምድር ተመራማሪዎችን ትኩረት ስቦ የኖረ መልከአ-ምድር ያለው አካባቢ ነው፡፡ ለዚህም ነው ዓለም አቀፍ የቅርስ ጥበቃ ሰኔ 20ቀን 2003 ዓ.ም በፓሪስ የተካሄደው 35ኛው ጉባኤ ኮንሶ በይፋ የአለም ህዝብ ቅርስ ሆኖ መመዝገቡን ያወጀው፤
2354 ስ.ኪ.ሜትር ስፋት ያለው የኮንሶ ወረዳ ትንግርት የሆነ መልከአ-ምድር ነው፡፡ኮንሶ ደረቅና ሁሉንም የአየር ጠባይ የሚያካትት ቦታ ነው፡፡ በወረዳው ሁለት የዝናብ ወቅቶች አሉ፡፡አንዱ በየካቲትና በመጋቢት መካከል ሌላው ደግሞ በመስከረምና በህዳር መካከል የሚከሰት ነው፡፡ መሬትን መጠበቅ የሚችሉት የኮንሶ ገበሬዎች በብዛት ማሽላና በቆሎ ያበቅላሉ ጤፍ፣ቡና ጥጥና አደንጓሬንም ሲያመርቱ ሙዝ ጫትና ፓፓዬም በአንዳንድ የኮንሶ አካባቢዎች ይበቅላሉ፡፡
ኮንሶ የተለያዩ የአርኪዎሎጂ ግኝቶችና ቅሪተ-አካሎች የሚገኙበት ስፍራ ነው፡፡በሆሞ ኢረክትስና አውስትሮሊፒቲከስ የሰው ዘር ዝርያዎች የተሞላ ምድር እንደሆነ አጥኚዎች ይናገራሉ፡፡
70 በመቶው የኮንሶ ምድር ቆላማ ነው ቀሪው 30 በመቶው ደግሞ ወይና ደጋማ የአየር ንብረት ሲኖረው አማካኝ አመታዊ የዝናብ መጠኑ ከ601-1200 ሚሊ ነው፡፡ ኮንሶ አሁን የብዙዎችን ትኩረት የሳበ የጎብኚ መዳረሻ የተመራማሪዎች የምርምር ቀጠና የኢትዮጵያውያን አያሌ እሴቶች መገለጫ መሆኑን አስመስክሯል፡፡

ኮንሶ ከዘመን ቀድሞ የነቃ…..የእውቀት ብቃታችን ማሳያ
ወደ ሁሉም የሃገራችን ክፍል የመጓዝ እድል የሚገጥመው ሰው አንዳች ተአምር ይመለከታል፡፡ በተለይም በአሁን ሰዓት ሃገራችን ከዳር ዳር ትኩረት ሰጥታ የሰነበተችበትን ተግባር የምታስመርቅበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ በየደረጃው ያለው አመራር ትኩረት ሰጥቶ ከየአርሶ አደሩ ማሳ የከረመበት ይህ ጉዳይ የተፋሰስ እና ተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ ነው፡፡ የተፋሰስና ተፈጥሮ ሃብት ስራ ማለት ለዘመናት የተራቆተውን ምድር ለማከም የሚደረግ የነፍስ አድን ርብርብ ነው፡፡ ይሄን ርብርብ አርሶ አደሩ ተገዶ ሳይሆን በሆታ አከናውኖታል፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ ከጥግ ጥግ ኮንሶን በሚመስሉ መልከአ-ምድሮች ተጥለቅልቃለች፡፡
የአፈር እና ውሃ ጥበቃ ስራ ከግብርና ስራችን አኳያ የምናልመውን ስኬታማ ምርታማነት ለማሳካት ብቻ የምናከናውነው ተግባር አይደለም አይዞህ ባይ የሌለው አፈር ለዘመናት ተጠርጎ ተራቁቷል፡፡ አፈር ህይወት ቢሆንም ለአፈር የሰጠንው ስፍራ አፈርን ከመጠበቅ አቀበንና ያልታቀበው አፈር ተጠርጎ ምርታማ እንዳንሆን አደረገን…..አፈርን ችላ ማለት ለድህነት እጅን መስጠት ነው፡፡ አፈር ያለው ይኖራል….አፈሩን መጠበቅ ያልቻለ፣አፈር መስሎ አፈር ውስጥ ይገባል…. አፈርን ስለመጠበቅ ጥበብን ለመቅዳት ወደየትም ማየት አያስፈልግም እዚሁ የሃገር ልጅ ዘመን የተሸገረ እውቀት አለ….

የኮንሶ ብሄረሰብ አፈርን የመጠበቅ ጥበብ ከተአምርነት አልፎ የዓለምን ትኩረት የሳበ አንድ የጥቁር ህዝቦች የኩራት መስህብ ለመሆን ችሏል፡፡ አፍሪካውያን ለግብርና ጥበብ ቀዳሚዎቹ ናቸው የሚለውን የመከራከሪያ ሃሳብ የሚያጸናው ይህ ኮንሶዎች ከአፈር ጋር ተያይዞ ያላቸው እውቀት ነው፡፡ የእርከን ጥበብ እንዲህ ሳይዘምን፣የአፈርና ውሃ ተመራማሪዎች ስለ አፈር እና ውሃ ያላቸው እውቀት ሳይልቅ፣ ኮንሶ የዚህ ጥበብ ሰርቶ ማሳያ ማእከል ነበር፡፡

የኮንሶ እርከኖች
የኮንሶ ደረቅ ካብ የያዘው ሰፊ መሬት 230 ስ.ሜትር ሲሆን ከምስራቅ ወደ ምዕራብ ከሰሜን ወደ ደቡብ ሰፊ መተላለፊያ ተዘርግቶበታል፡፡ በዋናው የሃገሪቱ ስምጥ ሸለቆ ውስጥ የሚገኘው ኮንሶ በሜዳማ ተዳፋት ቦታዎች መካከል ቀይ አሸዋ፣ ደለላማ ሸክላ ተከልሎ በደበና ወንዝ አካባቢ የካይሌ ወንዝን በማቋረጥ ዋናውን መንገድ በመያዝ የተቀየሰ ጥበባዊ ስራ ነው፡፡
ኮንሶ በጥንታዊ የድንጋይ ዘመን የነበረ የአሸዋ ዝቃጭ፣ደለልና ሸክላ አፈር የተከማቸበት ጥንታዊ ታሪክ ያለው ቦታ ነው፡፡ የኮንሶ መልከአ-ምድር በአንድ ወጥ የኮንሶ ድንጋያማ አካባቢ መገኘቱ ተመራጭ አድርጎታል፡፡ የደረቅ ድንጋይ እርከኑ በ1500 እና 2000 ሜትር ከፍታ ላይ በመገንባት የእርከን እርሻውን መንገድና ዋናውን የኮንሶ አካባቢ ይለያል፡፡
እርከኑ አፈሩን ከመጠረግ ይከላከላል፤ውሃ ያከማቻል፤የተረፈውን ውሃ ደግሞ ያስወግዳል፤ አፈር በመሸከም ለእርሻ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ ተራራዎቹ ለኮንሶ እርከን ዋና ገፅታዎች ሲሆኑ በደረቅ ድንጋይ የተሰሩ እርከኖች አፈሩ በደራሽ ውሃ እንዳይጎዳ ጭምር ይጠብቀዋል
በአጠቃላይ የእርከን ግንብ በተሳሰረ በተቆላለፈ መረብ ተያይዞ ይሰራል ጠምዛዛ ቦታዎችን ለማጠናከር 2ሜትር ቁመት ያለው መሰረት ይዘጋጃል፡፡ ሜዳዎቹ በጥንቃቄ ስለሚደለደሉ እርጥበትን እስከታች ድረስ ይይዛሉ፡፡ የእርከኑ ግንቦች 30 ሴንቲ ሜትር ስፋት ያላቸው ትንንሽ ክፍተቶችን ይኖራቸዋል፡፡ መውራጃዎችም የሚገነቡት በጥንቃቄ ነው፡፡በተመረጡ ድንጋዩች የተገነባው ቦታ የውሃ ግፊትንና ከባድ ማዕበልን ይከላከላል፡፡

የኮንሶ ጥብቅ ደኖች
የኮንሶ ባህላዊ ደኖች ጥብቅ ናቸው፡፡በኮንሶ ካሉ ጥብቅ ደኖች ለምሳሌ የባማለ'የካላ'የቁፋ የሚጠቀሱ ናቸዉ ፡፡ ኮንሶዎች በጥቅሉ ተፈጥሮን የመጠበቅ ባህላዊ እሴትን የተቸረ ህዝቦች ናቸው፡፡ ይኸ እሴት የላቀ እውቀት ሆኖ ከአለም ቅርስነት መዝገብ የሰፈረላቸው የኢትዮጵያን ገናናነት ማሳያ የሆኑም ናቸው፡፡ ይኸ ገናናነት ምናልባትም የሰው ልጅ ለኑሮው መሰረት ከሆነው የግብርና ስራ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው፡፡
ዛሬ ሃገራችን የተፈጥሮ ሃብቷን አድሳ ትርፍ አምራች አርሶ አደርችን አእላፍ ለማድረግ ሌት ተቀን እየተረባረበች ነው፡፡ ሁሉም የኢትዮጵያ አርሶ አደር እንደ ኮንሶ ምድሩን ከመከላት እንዲታደገው በየቀበሌው ከአመራር እስከ ባለሙያዎች ድረስ ከምድሩ ጋር በመታገል ተፈጥሮ የመታደግ ስራን ተያይዘውታል፡፡ ኮንሶ የዚህ ተግባር አርአያ ሕብረተሰብ ነው፡፡
                                              



ሐረ ሸይጣን ሐይቅ

ከአዲስ አበባ 142 ኪ.ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ሐረ ሸይጣን ሐይቅ ከስልጤ ዞን የተፈጥሮ መስህቦች አንዱ ነው፡፡ ከዞኑ መዲና ከወራቤ በ27 ኪ.ሜ ርቀት በስልጤ ወረዳ የሚገኘው ይኽ ሐይቅ ከአዲስ አበባ ሆሳእና በሚወስደው መንገድ ስልጤ ወረዳ ማዕከል አቀበት በ3.4 ኪ.ሜትር ርቀት ከዋናው መንገድ 1.2 ኪ.ሜትር ገባ ብሎ ይገኛል፡፡ ሐረ ሸይጣን ሐይቅ የሚገኚበት ቀበሌ አጎዴ ሎብሬራ ይባላል፡፡ በሰሜናዊ አቅጣጫ አይናጌ፣ ገሬራና ካብረ በቃ መንደሮች በደቡብ ደግሞ ሰነና ገሬራና በዜ ሳቦላ ቀበሌዎች በምስራቅ ደግሞ ሰነና ገራሬ ቀበሌና ቡልጋ መንደር እንዲሁም በምዕራባዊ አቅጣጫ የአጎዴ ቀበሌ ምንደር ያዋስኑታል::



ሐረ ሸይጣን ሐይቅ ከመሬት ንጣፍ በታች የሚገኝ ተፈጥሮአዊ መስህብ ሲሆን ከሃይቁ አፋፍ የሐይቁ ውሃ አስካለበት የታችኛው ክፍል ድረስ የ260 ሜትር ርቀት አለው፡፡ ከአፋር እስከ ውሃው ያለው ቨርቲካላዊ ርቀት 109 ሜትር ነው፡፡

የገበቴ ቅርፅ ያለው ሐረ ሸይጣን የስያሜው መነሻን በተመለከተ የተለያዩ አስተያየቶች ይቀርቡበቃል፡፡ “ሐረ ሸይጣን” የሚለው ቃል የኦሮምኛ ቃል ሲሆን “የሸይጣኖች እናት ወይም አውራ” እንደ ማለት ነው፡፡ ይኽው ቃል በስልጥኛ ቋንቋ ስያሜው “ሐር-አሽ-አጣን” ከሆነ እጣን አቀጣጥል የሚለው ትርጉም ይይዛል፡፡ ሐረ ሸይጣን እንዴት ተፈጠረ የሚለው ጥያቄ በብዙ የሳይንስ አዋቂዎች ዘንድ በእሳተ ጎሞራ የተፈጠረ ነው የሚሉ አስተያየቶች ቢቀርቡም በሐይቁ ዙሪያ በአካባቢው ላይ በስልጤ ዞን ባህል ቱሪዝም አማካኝነት በተደረገ ጥናት አንዳንድ የሃገር ሽማግሌዎች ሐይቁ ኑር ሆሴን ከሚባሉ የእስልምና አባት (ወሲይ) ጋር በተያያዘ እንደተፈጠረ ይገልፃሉ፡፡

እንደ ሃገር ሽማግሌዎቹ ገለፃ ኑር ሁሴን ከሩቅ ቦታ በእንግድነት ሲመጡ አሁን ሐይቁ ወደ አረፈብ ስፍራ የነበረ መንደር ጎራ ይላሉ፤ በከተማዋ የነበሩ ሰዎች ግን ኑር ሁሴንን በእንግድነት ሊቀበሏቸው አልፈቀዱም እናም ኑር ሁሴን አዝነው ተራገሙ፡፡ ያ- እርግማን ያንን መንደር ከትንሽ ውሃ ቀስ እያለ በመሙላት አስመጠውና የዛሬው ሐረ ሸይጣን ሐይቅ ተፈጠረ ይላሉ፡፡ ከሐረ ሸይጣን ሐይቅ አናት ሆነው ድንጋይ ቢወረውር ወደ ሐይቁ ማስገባት የሚቻል አይደለም፡፡ ይኽንን በተመለከተ አንዳንዶች በፍፁም ማስገባት አይቻልም ሲሉ ሌሎች ደግሞ የሐይቁ ቅርፅ ገበቴ ስለሚመስል ለማስገባት ከ230 ሜትር በላይ ድንጋይ የመወርወር አቅምን ስለሚጠይቅ ነው ይላሉ፡፡ በየትኛውም ትርጓሜ ግን ብዙዎቹ ወደ ሐይቁ ከሐይቁ ጫፍ ሆነው የወረወሩት ድንጋይ ውሃው ላይ ሲያርፍ አልታየም፡፡

በ17.6 ሄክታር ላይ ያረፈው ይኽ ሐይቅ ወቅትን ጠብቆ ቀለሙን መቀያየሩ ደግሞ ሌላው ትንግርት ነው፡፡ ቀይ አረንጓዴ ሰማያዊ ከመሆሙ ጋር ተያይዞ በአካባቢው ህብረተሰብ ዘንድ በተለይም ቀደም ባለው ግዜ የተለያዩ ትርጉም ይሰጠው ነበር፡፡ ከውሃው ቀለም በመነሳት ቀጣዩ ወቅት ረሃብ ነው ጥጋብ ነው በሚል ይተነብዩበታል፡፡ የውሃው ቀለም የመቀያየሩ ሚስጥር በዙሪያው ከሚገኙ ማቴሪያሎች ነፀብራቅ በመነሳት ነው ይላሉ፤ የሳይንስ ባለሙያዎች ይኸም አፈሩ እፅዋቱና ደኑ ከሰማይዋ ፀሐይ ነፀብራቅ ጋር ተዋህደው የሚፈጥሩት ክስተት ነው፡፡

ሐረ ሸይጣን ሐጥቅ ዙሪያው በመስኸብ የተሞላ ነው፡፡ አነስተኛ ተራሮች፣ ተፈጥሮአዊ ዋሻዎችና ፍል ውሃዎችን ጨምሮ በርካታ ተፈጥሮአዊ መስኽቦች ይገኙበታል፡፡ የሐይቁን በእሳተ ጎሞራ መፈጠር የሚያሳዩ በርካታ ምልክቶች እንዳሉ አንዳንድ ጥናቶች አስፍረዋል፡፡ ሐረ ሸይጣን ሐይቅ በዙሪያው በርካታ የመስኽብ ሃብቶች በመኖራቸው ለቱሪዝም ኢንቨስትመንት ምቹ ቀጠና ነው፡፡ በተለይም ዋና መንገድ ስር መኖሩ ለአካባቢው ልማት ተስፋ ስለመሆኑ አያጠራጥርም፡፡



የውሃ ቱሪዝም በኢትዮጵያ

ውሃ ለእርካታ ቅርብ ከሚባሉ የተፈጥሮ ስጦታዎች አንዱ ነው፤ ቅርብነቱ ግን ይጎላል፡፡ ጥም የማርካቱን ያክል እይታ ላይም እንዲሁ አንዳች ስሜት ይፈጥራል፡፡የውሃ ቀለም እራሱ ውሃን ብቻ መምሰሉ መስኽብ ነው፡፡ አያሌዎችን በማዝናናት ወደር ያልተገኘለት ውሃ አሁን የዓለም ውድ የመዝናኛ ስፍራዎች ሰፈራቸውን ስሩ ለማድረግ እንዲገደዱ ያደረገ የተፈጥሮ ሃብት ነው፡፡

የዓለም የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ውሃ ቱሪዝም ዘርፍን እውቅና ከመስጠት አልፎ ለአያሌዎች በረከት ለመሆን የቻለ ግዙፍ የቱሪዝም ጥላ ሲል ፈርጆታል፡፡ ለብዝሃ-ጎብኚ/mass tourism/ ምንጭነት በማገልገል ረገድም የውሃ ቱሪዝም የሚጫወተው ሚና ቀላል አይባልም፡፡

በጀልባና በመርከብ በመሆን አልያም በአነስተኛ መቅዘፊያዎች በመንሳፈፍ የተጀመረው የውሃ ቱሪዝም ዘውግ ዛሬ ለበርካታ የቱሪዝም አይነቴዎች/types/ መገለጫ ሆኗል፤ በባህላዊ መልኩ አሳ የማስገር ጥበብ አዝናኛ ሆኖ የቱሪዝም መስኩን ሲቀላቀል የተመደበው ከውሃ ቱሪዝም ዘርፍ ነበር፡፡ ባህር አቋራጭ ዋና፣ የጥልቅ ውሃ ውስጥ ሽርሽር፣ የውሃ ውስጥ እንስሳት ጉብኝት/aquatic animal tourism/፣ የውሃ ዳርቻ ስፖርታዊ መዝናኛዎች/beach recreation sport site/፤ ከቀን ወደ ቀን ውሃን መሰረት ያደረጉ የቱሪዝም ዘርፎች ቁጥራቸው እየጨመረ መጥቷል፡፡

እንደ ቱሪዝም ምርት ጥናት ባለሙያዎች/tourism product development professionals/ ገለጻ የውሃ ቱሪዝም/water tourism/ ፣የጀብድ ቱሪዝም/adventure tourism/ ፣የእንሰሳት ቱሪዝም/aquatic animal tourism/ እና የመዝናኛ ቱሪዝምን/recreation  tourism በማካተት በቱሪዝም ምርትነት የታጨቀ ዘውግ ነው፡፡ ይህ እንግዲህ ለጥናትና ለምርምር የሚደረጉ የቱሪዝም አይነቶችን ከዉሀ ቱሪዝም ጋር ሳንቀላቅል ነው፡፡ በሌላ በኩል ከቅርብ ግዜ ወዲህ የቱሪዝም ምርት ልይት ባለሙያዎች/ tourism product identification professionals/ የውሃ ዳር ዳርቻ መዝናኛዎችን/beach recreation/ ከውሃ ቱሪዝም ዘውግ የሚመደብ እና ህልውናው ውሃን መሰረት ያደረገ ነው ወደሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል፡፡

የሃገራችን የውሃ ሃብት ለቱሪዝሙ ኢንዱስትሪያችን ረብ ያለው አስተዋጾ ባይወጣም የአፍሪካ የውሃ ማማ በሚል ቅጽል ስሟ የምትታወቀው ኢትዮጵያ የበርካታ ሀገር አቋራጭ ወንዞች ሰፋፊ ሃይቆችና ማራኪ ፏፏቴዎች መገኛ ምድር ናት፡፡ ከቅርብ ግዜ ወዲህ በርካታ መዝናኛዎችን በማስጠጋት ለሪዞርት ኢንቨስትመንት የጀርባ አጥንት እየሆነ የመጣው የጣና ሃይቅ ዙሪያውን የመዝናኛ ማእከል ከመሆን በአለፈ ባህር ዳር ከተማን የጎብኚ መዳረሻ እንድትሆን በማድረግ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡ አማካኝ ጥልቀቱ 15 ሜትር የሚደርሰው ጣና 80 ኪ.ሜትር ያክል ርዝመት 66ኪ.ሜ ያክል ስፋት አለዉ

በርካታ ሐይቆች ያስጠጋዉ የታላቁ ስምጥ ሸለቆ ምድር በሃገር ዉስጥ ጎብኚዎች ዘንድ ተወዳጅ የሆኑ የመዝናኛ ሐይቆች የሚገኙበት ነዉ:: ለአብነት የእንስሳት ቱሪዝምን በዉሃ ላይ ይዞ የሚገኘዉ የጫሞ ሐይቅ በጎብኚዎች ዘንድ ከሚፈለጉ መዳረሻዎች አንዱ ሆናDEል:፡ 32ኪ.ሜ ርዝመት እና 13 ኪ.ሜ ስፋት ያለዉ ጫሞ አማካይ ጥልቀቱ 10 ሜትር ሲሆን አንጁሌ የተባለ የአዞ መጠለያ ደሴት ይገኝበታል፡፡ ሻላ አባያታ እና አባያ በፓርክ ቅጥር ዙሪያ የሚገኙ የመዝናኛ ሐይቆች ሲሆኑ፤ የላንጋኖ ሐይቅ ደግሞ በሐይቅ ዳር ዳርቻ መዝናኛዎች የሚታወቅ የእረፍት ቀናት ማሳለፊያ የሆነ የውሃ ቱሪዝም መስህብ ነው፡፡

የውሃ ሃብት የከተማ ገጽታን/ image building/  በመቀየር በኩል ያለው ፋይዳም በሃገራችን ከተሞች ዘንድ ውሃ ተጽእኖ ማሳደር የቻለ የተፈጥሮ ሃብት እየሆነ መጥቷል፡፡ ከአስራ አምስት ዓመታት በፊት የሐይቅ ሃብት ያላቸው ከተሞች መገለጫ ወባና የቢንቢ ትንኝ ሆኖ ለመኖሪያ እንኳን እምብዛም የማይመረጡ ነበሩ፡፡ በአሁኑ ወቅት በተቃራኒው እነዚህ ከተሞች በከፍተኛ ሁኔታ ተፈላጊ በመሆን ለኑሮ ምቹ፣ ውብ፣ ለንግድና ለቱሪዝም ተመራጭ ከተማ ለመሆን ችለዋል፡፡ በኮንፈረንስ ቱሪዝም ማእከልነትም ቢሆን በተመራጭነት ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዙ ናቸው፡፡ ይህም የውሃ ሃብት በከተሞቻችን  እድገትና ኢኮኖሚ ላይ እየተጫወተ ያለው ሚና እያደገ መሆኑን ያሳያል፡፡

የሐይቅ ከተሞች/city of lake’s/ በሚል የሚገለጹት እና በቱሪዝም ኢንዱስትሪ እየገነኑ የመጡት ባህር ዳር፣ ሃዋሳና ቢሸፍቱ ተፈጥሮ የለገሰቻቸውን ውሃ ሃብት ለውሃ ቱሪዝም በመጠቀም እና ሴክተሩ ከፈጠረው መነቃቃት በመነሳት በሃገሪቱ ምርጥ የሚባሉ ሪዞርቶች መብቀያ ሆነዋል፡፡ በዚህ ተነሳሽነት እነዚህ ከተሞች ለነዋሪዎቻቸው እንዲመቹ፣ በጎብኚዎች ዘንድ ተመራጭ እንዲሆኑ ለማድረግ የየከተሞቹ አስተዳደር ዘርፈ ብዙ ስልቶችን በመንደፍ በርካታ ስራዎችን እየሰራም ይገኛል፡፡

በተቃራኒው እንደ ወሎው ሐይቅ ሐይቅ፣ ሐሸንጌ፣ ሐሮ ሸይጣን፣ ቢሻን ዋቃ፣ ሐሮ ደንበል፣ ሐሮማያ፣ ዘንገና፣ በሰቃና ቆቃ የመሳሰሉት ሐይቆች በአቅራቢያቸው ላሉ ከተሞች ይቅርና በዙሪያቸውም ቢሆን የተፈጥሮ ገጸ-በረከትነታቸውን የሚመጥን ኢንቨስትመንት አልተካሄደባቸውም፡፡

የረጃጅም ወንዞች መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ በዓለም በርዝመቱ አንደኛ የሆነው የናይል ወንዝ መነሻ ምድር ናት፤ ከውሃ ቱሪዝም ጋር በተያያዘ የአባይ ተፋሰስ ሃገራት በተፋሰሱ ወንዞች ላይ አያሌ ተግባራትን በማከናወን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን አረጋግጠዋል፡፡ የወንዝ ላይ የጀልባ ቀዘፋ መዝናኛ እስከነጭራሹ በማይታወቅባት ሃገራችን እንደ ዋቢሸበሌ፣ ተከዜ፣ ጊቤ፣ ጎጀብ፣ አኮቦ፣ ብላቴ፣ አዋሽና ገናሌ የመሳሰሉ ወንዞች እየጋለቡ ይፈሱባታል፡፡ በአናቱ ላይ የውሃ ትራንስፖርትን የሚያስተናግድ ብቸኛ ወንዝ ባሮ ነው፤ ባሮም ቢሆን ጀልባ ከነጓዙ የሚወጣበት በክረምት ነው፡፡ አዋሽ ዳርቻውን ለመስኖ እርሻ እንደዋለ ሁሉ ባሮም ቢሆን ለመዝናኛ እና ማረፊያ አገልግሎት መዋል ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ ይህ የመዝናኛ ቀጠና ግን በሃሳብ የቀሩ አነስተኛ የሻይ አቅርቦት ያላቸው የዛፍ ስር መዝናኛዎችን የያዘ እንጂ ለባሮ ግርማ ሞገስ የሚመጥን ግዙፍ የሪዞርት መዳረሻ አይደለም፡፡ በሌላ በኩል በአዋሽና አባይ ወንዝ ዳርቻዎች ብቅ ብቅ ማለት የጀመሩት የሎጅ ኢንቨስትመንቶች ወንዞቻችን ከውሃ ቱሪዝም ዘርፍ ተጠቃሚ እንደሚያደርጉን የሚያሳዩ የተስፋ ፍንጣቂዎች ናቸው፡፡

እንደ ጢስ አባይ፣አጆራና አዋሽ የመሳሰሉ ፏፏቴዎች ከእልፍ የሃገራችን ድንቅ ፏፏቴዎች ጥቂቶቹ ናቸው ሁሉም ለውሃ ቱሪዝም ዘርፍ ወደ ገንዘብ ሊቀየሩ የሚችሉ መስህቦች ይሁኑ እንጂ አንዳችም ያልተጠቀምንባቸው በእጅ ያሉ ወርቆች ናቸው፡፡ ውሃ በታዳሽ ሃይልነቱ የመጪው ግዜ የሃገራችን የሃይል ችግር መቅረፊያ እንዲሁም በዓመት እስከ ሶስት ግዜ በማምረት የምግብ ዋስትናችን ማረጋገጫ ይሆናል ብለን ከሰነቅንው ተስፋ እና ወደ ተስፋው ለመድረስ ከምናደርገው ጉዞ ባሻገር የቱሪዝም ኢንዱስትሪያችን ምርት ሆኖ በርካታ የውጪ ምንዛሪ የምናፍስበት ግዜ ሩቅ አይሆንም፤ ግን ከሰራንበት ነው…..ሊያውም ጠንክረን ከሰራን!!! 

No comments:

Post a Comment