Wednesday, July 8, 2015



ኢትዮጵያ የ2015 የዓለም ምርጥ የቱሪዝም መዳረሻ፤
የአውሮፓ የቱሪዝምና ንግድ ምክር ቤት ኢትዮጵያን የባህላዊ ቱሪዝም መዳረሻ ብሎ መርጧታል፡፡ ይህው ካውንስል በ2015 የዓለም ምርጥ የቱሪዝም መዳረሻ በሚልም ነው የመረጣት፡፡ ይህን ሽልማት በማስመልከት የኢፊዲሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ አሚን አብዱልቃድር ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ሙሉጌታ ሰይድና የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ታደሰ ዛሬ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ሽልማቱን በይፋ ሐምሌ 3 ቀን 2007 ዓ.ም. በብሔራዊ ቤተ መንግስት በሚደረግ ስነ ስርዓት እንደምንቀበል ገልጸዋል፡፡
ከዚህ በፊት ለዙምባቤ በተመሳሳይ መልኩ ይህንን ዓመታዊ የዓለም የተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻነት ሽልማት በማግኘት ኢትዮጵያ ሁለተኛዋ አፍሪካዊት ሀገር ስትሆን በዘንድሮው ሽልማት ከ31 በላይ ሀገራት ዕጩ ነበሩ፡፡ ይህንን ሽልማት በብሔራዊ ቤተ መንግስት በሚደረገው ስነ ስርዓት ስንቀበል ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ በአመራርነት ለኢትዮጵያ ቱሪዝም ልማት ላበረከቱት የላቀ የአመራርነት ሚና እውቅና የሚቸራቸው ይሆናል፡፡
ሽልማቱን ለመስጠት ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣው የአውሮፓ የቱሪዝምና ንግድ ምክር ቤት የልኡካን ቡድን በኢትዮጵያ የአምስት ቀናት ቆይታው በኢትዮጵያ የሚገኙ መዳረሻዎችንና ባህላዊ እሴቶችን የሚጎበኝ ይሆናል፡፡